አማራ ክልል መምህራን ማህበር 14ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ
የአማራ ክልል መምህራን ማህበር 14ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ በባህርዳር ከተማ ማካሄድ ጀምሯል፡፡
በጠቅላላ ጉባኤ መክፈቻ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን፣ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ማተብ ታፈረ፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዘዳንት ዶ/ር ዮሀንስ ባንቲ፣በየደረጃው የሚገኙ የመምህራን ማህበር አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን የሀገራችን የትምህርት ዘርፍ ለውጥ ከሚያስፈልገው ዘርፍ አንዱ በመሆኑ የስርአተ ትምህርት ለውጥ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የስርአተ ትምህርት ማሻሻያው በተገቢው ሁኔታ የተገነባ ትውል ለመፍጠር የመምህራን ሚና የጎላ በመሆኑ አዲሱ የክልሉ መንግስት ለትምህርት ትኩረት ይሰጣል ያሉት ኃላፊው ከመምህራን ጋርም በቅርበት በመወያየት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ከልብ እንሰራለን ብለዋል፡፡
ክልሉ አሁን የህልውና ዘመቻ ላይ በመሆኑ ማህበሩና አባላቱ በሚችሉት ሁሉ የህልውና ዘመቻውን እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በፕሮግራሙ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዘዳንት አቶ እናውጋው ደርሰህ ለአንድ ሀገር አጠቃላይ እድገት መሰረት የሆነውን ትምህርት ውጤታማ ይሆን ዘንድ የመምህራን ሚና ተኪ የለውም፡፡ ይህን የተረዳው በየደረጃው ያለው የመምህራን ማህበር የመምህራንን ደህንነት ተከብሮ መብትና ጥቅማቸው ተረጋግጦ ስራቸውን በተረጋጋ ሁኔታ እንዲሰሩ ማህበሩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ውይይት በማድረግ የመምህራን ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ በትኩረት ተሰርቷል ብለዋል፡፡
የመምህራን ደሞዝ ማሻሻያና የመምህራን መኖሪያ ቤት በክልል ደረጃ ደንብ ወጥቶለት በስራ ላይ እንዲውል መሰራቱን አውስተው በአጠቃላይ በየደረጃው ያለው የማህበሩ መዋቅር የመምህራንን አስተዳደራዊ ችግሮች እንዲፈቱ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑ ታውቋል፡፡
በአሁ ጊዜም አሸባሪው ቡድን በክልላችን ያደረሰውን ጥፋት ማህበራችንና መላው አባላችን የሚያግዙት ሲሆን ከመንግስትና ከመላው ማህበረሰብ ጋር በጋራ በመሆኑ ኃላፊነታችን እየተወጣን ነው ብለዋል፡፡
ጉባኤው የ5 ዓመት የስራና የበጀት እቅድ አፈፃፀም ቀርቦ ውይይት እየተካሄደ ሲሆን በተመሳሳይ ሁሉም ዞን መምህራን ማህበር ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡በመጨረሻም የክልሉ መምህራን ማህበር አስፈፃሚ አካላት ምርጫ እንደሚካሄደም ከወጣው መርሃ ግብር ማወቅ ተችሏል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ Amhara National Regional State Education Bureau
በዌብሳይት https://www.anrseb.gov.et/
በቴሌግራም https://t.me/anrse
ፌስቡክ https: Amhara Education Bureau

By awoke

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *