የትምህርት ስራ ውድቀቶች ሁሉ የቅድመ ዝግጅት መጓደል ነው፡፡ ዶ/ር ማተብ ታፈረ
================================================================
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ9 ወራት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ፣ በ2014 የትምህርት ዘመን ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች የቅድመ ዝግጅት እና በሌሎች ጉዳዮች ከሚያዝያ 26-27/2014ዓ.ም በደሴ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡ ዛሬ በተጠናቀቀው የእቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ የትምህርት ስራዎች ውድቀቶች ሁሉ በቂ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ባለመስራት የመጡ መሆናቸውን የትምህርት ቢሮ ኃላፊው ማተብ ታፈረ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ችግር በራሱ ውድቀት ሊሆን አይችልም ያሉት ቢሮ ኃላፊው ይልቁንስ ችግር ውድቀት የሚሆነው ለችግሩ በቂ ቅድመ ዝግጅት አለማድረግ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም በትምህርት ስርዓቱ ውድቀትን ላለማስተናገድ ቢሮው ወደ ውስጥ በመመልከት አዲስ ምዕራፍ ጀምሯል ብለዋል፡፡
ችግሮችን በቅድመ ዝግጅት መመከት ባለመቻላችን ውድቀትን እያስተናገድን ለውድቀቱም ውጫዊ ምክንያት በመደርደር ዘላቂ መፍትሄ ለህዝባችን ማምጣት ስለማንችል ለችግሮች ሁሉ መፍትሄዎች እኛው መሆናችን አውቀን በትጋትና በቁርጠኝነት ልንሰራ ይገባል ተብሏል፡፡
በቀጣይ ለሚገጥሙን ችግሮች ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ አሸናፊ መሆን እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
በትምህርት ዘመኑ የትምህርት ተቋሙ በበርካታ ፈተናዎች ያለፈ መሆኑን የተናገሩት ቢሮ ኃላፊው በኮቪድ-19 ፣በተማሪ ምዝገባ፣ በጦርነቱና በ2013 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ከብሔራዊ ፈተና የተማሪዎች ውጤት ጋር በተያያዘ ያጋጠሙትን ፈተናዎች ለመወጣት ሰፊ ስራ መሰራቱን ነው ኃላፊው የተናገሩት፡፡
እድሜው ለትምህርት የደረሰ ህፃን ወደ ትምህርት ቤት መምጣት ችግር ሊሆን አይገባም ነበር ያሉት ኃላፊው ለሚመለከተው አካል ሁሉ የትምህርትን ጠቀሜታ ቀድመን ባለማስረዳት የመጣ ችግር ነው ብለዋል፡፡
በምስራቅ አማራ በጦርነቱ ምክንያት የገጠመን ችግር በተሰራው ሰፊ ስራ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማደራጀትና ትምህርት ለማስጀመር መቻሉ መልካም ቢሆንም አሁንም ሰፊ ንቅናቄ በማድረግ ትምህርት ቤቶችን ወደ ነበሩበት መመለስ ይገባል ተብሏል፡፡
የ2013 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ተማሪዎች ውጤት መቀነስ ጋር በተያያዘ በተደረገው ሰፊ ርብርብ መልካም ውሳኔ መወሰኑን ተጠቁሟል፡፡
ለቀጣይ 2014 የትምህርት ዘመን ብሔራዊ ፈተና ተፈታኞችና በድጋሚ ለሚፈተኑ ተማሪዎች በቂ ቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመስራት ውጤታማ መሆን እንደሚገባ በመድረኩ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በመጨረሻም በ2013 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ወስደው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች የገንዘብ ሽልማት የተበረከተ ሲሆን ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ የልዩ ፍላጎት እና የወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ ዞን ተማሪዎች ልዩ ተሸላሚዎች ነበሩ፡፡
ለተጨማሪ መረጃ
1. በዌብ ሳይት ገጻችን http://www.anrseb.gov.et/
3. በፌስ ቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau
4. በቴሌግራም ቻናላችን t.me/anrse
ያግኙን!!

By awoke

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *