በአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ የተገነባው የደብረ ማርያም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።
የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ያስገነባው የደብረ ማርያም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠናቅቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
በ2008 ዓ.ም የተመሠረተው የደብረ ማርያም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመማር ማስተማሩ ሥራ አመች አልነበረም። በጠባብ ግቢና ደረጃውን ባልጠበቀ ግንባታ ውስጥ ሕጻናት ሲማሩ ቆይተዋል።
በደብረ ማርያም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን የሚከታታሉ ተማሪዎች ከአሁን በፊት በጭቃ ክፍል ባልተመቸ ትምህርት ቤት ሲማሩ እንደነበር ነው የተናገሩት። አሁን ላይ ትምህርት ቤቱ በመሻሻሉ ትምህርታቸውን ለመከታተል የተመቸ እንደሚኾን ነው የተናገሩት። በበጋ አቧራው በክረምት ደግሞ ጭቃው ሲያስቸግራቸው እንደነበርም ገልጸዋል።
በትምህርት ቤቱ ልጆቻቸውን ልከው የሚያስተምሩ ወላጆችም በትምህርት ቤቱ መገንባት ደስተኞች መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
የደብረ ማርያም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ወይዘሮ እንይሽ በላይ ትምህርት ቤቱ ለመማር ማስተማር የተመቸ እንዳልነበር ነው የገለጹት።
የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ትምህርት ቤቱን ለማዘመን ባቀረበላቸው ጥያቄ መሠረት ትምህርት ቤቱ መገንባቱን አመላክተዋል። ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተማሪዎችን በጥራት ማስተማር እንደሚጀምሩም ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቱ አሁንም የመብራት ችግር እንዳለበት ነው የተናገሩት። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የመብራት ችግራቸውን እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።
ድርጅቱ አምስት የመማሪያ ክፍልና ሦስት የአሥተዳደር ክፍል ጨምሮ ሌሎች ግንባታዎችን ነው ያከናወነው።
የአማራ ክልል መንገድ ሥራዎች ድርጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ግርማው በለጠ ትውልድ የሚቀረጽበት ተቋም መገንባት ደስተኛ እንደሚያደርግም ገልጸዋል። ድርጅቱ በማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራው እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
ሌሎች ድርጅቶችም የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅትን አርዓያነት በመከተል በማኅበረሰብ አገልግሎት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የደብረ ማርያምን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ለመገንባት 5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ገደማ ወጪ ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ባየ አለባቸው የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ላደረገው መልካም ተግባር አመስግነዋል። የአማራ መንገድ ሥራዎች በከተማ አሥተዳደሩ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑን ገልጸዋል። ድርጅቱ በቀጣይ በመልካም ተግባሩ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል። ሌሎች የልማት ድርጅቶች በከተማ አሥተዳደሩ የጎደሉ የልማት ሥራዎችን እንዲሞሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በከተማዋ ቤተ ሙከራ የሌላቸው፣ ግቢያቸው ማራኪ ያልኾነና ያልተመቹ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ የተናገሩት ምክትል ከንቲባው ችግሮችን ለመፍታት የልማት ድርጅቶች እና ኅብረተሰቡ በጋራ በመኾን መሥራት ይገባል ብለዋል።
ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጋር በመኾን በትጋት እንዲሠራ ጠይቀዋል። ከትምህርት ቤቱ የቀረበውን ጥያቄ እንደሚፈቱም ቃል ገብተዋል። የከተማዋ ባለሀብቶችም መልካም ተግባር እየፈፀሙ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
የትምህርት ቤቶችን ጥራትና ደረጃ ለማሻሻል በጋራ መሥራት ይገባልም ነው ያሉት።
በባሕር ዳር ከተማ ለከተማዋ የማይመጥኑ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ተመላክቷል።
ኹሉም የልማት ድርጅቶች እንደ አማራ መንገድ ሥራዎች ኹሉ ትምህርት ቤቶችን በመሥራት በከተማዋ የሚስተዋለውን የትምህርት ቤት ጥራት ችግር እንዲቀርፉ ጥሪ መቅረቡን አሚኮ ዘግቧል።

By awoke

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *