በአሜሪካ ቨርጂኒያ የምትኖረው ኢትዮጵያዊቷ የ15 ዓመት ታዳጊ በዘጌ ከተማ ለሚገኘው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገች፡፡
==========================
በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት የምትኖረው የ11ኛ ክፍል ተማሪዋ ቤተልሔም አስፋው በደብረ ብርሃን ከተማ በመጠለያ ጣቢያ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች እና የመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት ላለባቸው ትምህርት ቤቶች ድጋፍ ለማድረግ 300 ሺህ ብር አሰባስባ ነው ወደ ሀገሯ ኢትዮጵያ ብቅ ያለችው።
ታዳጊዋ ቤተልሔም በዘጌ አንደኛ ደረጃ ሙሉሳይክል ትምህርት ቤት በመገኘት ባስተላለፈችው መልዕክት ከአሁን በፊት ባደረገችው ቅኝት ከፍተኛ የመማሪያ ቁሳቁስ ጉድለት መመልከቷን ተናግራለች።
 
“የመማሪያ ቁሳቁሱ ሕይወት በመቀየር ረገድ ትልቅ አስተዋጽዖ ስላለው መጻሕፍቱን በመጠቀም ጠንክራችሁ መማር ይጠበቅባችኋል” ነው ያለችው።
ታዳጊዋ 156 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የመማሪያ ቁሳቁስ ነው ለዘጌ አንደኛ ደረጃ ሙሉሳይክል ትምህርት ቤት ድጋፍ ያበረከተችው።
በዘጌ ከተማ የሚገኘው አንደኛ ደረጃ ሙሉሳይክል ትምህርት ቤት የሚያስፈልገውን የመማሪያ ቁሳቁስ በመለየት ድጋፍ ማድረጓን ታዳጊዋ አስረድታለች። 1 ኮምፒውተር፣ 982 አጋዥ መጻሕፍት፣ 1 ፕሪንተር፣ ለተግባቦት የሚውል ዲሽና ቴሌቪዥን ናቸው ለትምህርት ቤቱ ድጋፍ ያደረገችው። በቀጣይ ድጋፍ ለማድረግም ታዳጊዋ እቅድ እንዳላት ተናግራለች።
ታዳጊዋ በደብረ ብርሃን በመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ታዳጊ ሴቶች የንጽሕና መጠበቂያ ድጋፍ ማድረጓን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በትምህርት ቤቱ የአንደኛ ክፍል ተማሪ የኾነችው ፈትለወርቅ አበባው ለትምህርት ቤታቸው የተበረከተላቸውን መጽሐፍት በአግባቡ እንደምትጠቀም ተናግራለች። የመጫወቻ ጊዜዋን በመቆጠብ ለንባብ እንደምታውለውም ነው ተማሪዋ የተናገረችው።
የዘጌ አንደኛ ደረጃ ሙሉሳይክል ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ደመቀ ወርቄ ታዳጊዋ ያበረከተችላቸው መጻሕፍት በትምህርት ቤታቸው የሚስተዋለውን የአጋዥ መጻሕፍት እጥረት በመቀነስ በኩል ትልቅ ድጋፍ መሆኑን ተናግረዋል። የትምህርት ቤታቸው ተማሪዎች አጋዥ መጻሕፍትን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እንደሚሰጡም አስረድተዋል። ተማሪዎች ቅዳሜና እሑድን ጨምሮ አጋዥ መጽሐፍትን በመዋስ እንዲጠቀሙ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻቹላቸውም ጠቁመዋል።
ዘገባው የአሚኮ ነው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ለማግኘት የሚከተሉትን ማስፈንጠሪያዎች ይጫኑ
1. በዌብ ሳይት ገጻችን http://www.anrseb.gov.et/
3. በፌስ ቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau
4. በቴሌግራም ቻናላችን t.me/anrse
ያግኙን!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *