ስፕላሽ ኢንተርናሽናል ድርጅት በባህርዳር ከተማ ባሉ ትምህርት ቤቶች የእጅ መታጠቢያና መፀዳጃ ቤት ገንብቶ ዓለም አቀፍ የእጅ መታጠብ ቀን አከባበር ዝግጅት ላይ አስረከበ።
ዓለም አቀፍ የእጅ መታጠብ ቀን በባህርዳር ከተማ መስከረም 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የፌደራል ጤና ሚኒስትርን ጨምሮ የክልሉ የትምህርትና ጤና ቢሮ ተወካዮች እና የአጋርና ባለድርሻ ድርጅት ተወካዮች በተገኙበት “የእጅ ንፅህናን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በአንድነት እንስራ”! በሚል መሪ ቃል በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
የዓይነ-ምድር አወጋገድ ሥርዓትን በማሻሻልና የከርሰ ምድር ውሃ ብክለትን በመከላከል ጤናማ ማህበረሰብ በመገንባት ረገድ አጋር ድርጅቶች እያደረጉት ያለው የላቀ ሚና የሚደነቅ ተግባር መሆኑንና ይህም በሁሉም አካል ዘንድ ትኩረት ተሰጥቶት በቅንጅት መሰራት እንዳለበት ተገልጿል።
እጅን በዉሃና በሳሙና በአግባቡና በወሳኝ ጊዜያት መታጠብ ተቅማጥን በ 50 በመቶ እንዲሁም አጣዳፊ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎችን በ 25 በመቶ በመቀነስ ህይወትን ለማዳን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እንደ ኮቪድ ፡ ኢንፍሉዌንዛ እና የመሳሰሉትን ተላላፊ በሽታዎች እንዳይሰራጩ ይከላከላል ፡፡
የበሽታዎቹን የመተላለፊያ ሰንሰለት ለመቁረጥ ዉሃን እና ምግብን በጥንቃቄ መያዝ ፤ የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ፡ የዝንቦችን እና ትንኞችን ንክኪ መቀነስ፣ የግል ንጽህናን መጠበቅ፣የአይነ ምድር አወጋገድ ስርአትን ማሻሻል፣ የአካባቢ ጸዳትን በግልም ሆነ በጋራ መጠበቅ ወሳኝ ተግባራት ናቸዉ ፡፡ በተለይም እጅን በዉሃና በሳሙና መታጠብ ቀላል፣እርካሽና ፍቱን የሆነ ተለላፊ በሽታዎች የመከላከል ዘዴ ነዉ ፡፡
ነገር ግን እጅን በሳሙና እና በዉሃ በወሳኝ ጊዜያት በአግባቡ የሚታጠበዉ የሀገራችን የህዝብ ቁጥር አነስተኛ ነዉ፡፡ ይህንንም በመረዳት በአገራችን በኢትዮጵያም የእጅ መታጠብን ባህል ከፍ ለማድረግ በጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር ዉስጥ በማካተት በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ና በጤና ልማት ሰራዊት አደረጃጀት በመጠቀም ሽፋኑን ከፍ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ
እጅን በዉሃና በሳሙና መታጠብ ብዙ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል መሆኑን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ከትምህርት ተቋማት ጋር በጋራ በመስራት መልእክቱን በፍጥነትና በዉጤታማነት ወደ ህብረተሰቡ ለማስረስ ያስችላል፡፡ ይህን ወሳኝ ተግባር የተገነዘበዉ SPLASH የተሰኘዉ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከመንግስት ጋር በመተባበር እንደመጀመሪያ በ 3 የትምህርት ተቋማት የእጅ መታጠቢያ ሲንኮች፣ ንጹህና የተጣራ የመጠጥ ዉሃ የሚያቀርቡ መሳሪያዎች፣ ለልዩ ፍልጎት ተማሪዎች እና ለሴት ተማሪዎች መፀዳጃ ቤቶች፣ ለሴት ተማሪዎች የሻወር አገልግሎት በመገንባት አስረክቧል፡፡ ለወደፊትም በባህር ዳር ከተማ ባሉ ተጨማሪ 13 ት/ቤቶች ስራዉ እንደሚቀጥል መግባባት ላይ ተደርስዋል።
ድርጅቱ የእጅ መታጠቢያ ሲንኮችን በብርቱካናማ ቀለም እንዲሆኑ በማድረግ ከፊት ለፊታቸዉ መስታዉት በማስቀመጥ፣ የእጅ አስተጣጠብ ዘዴ የሚያሳዩ ምስሎችን በማስቀመጥ ልጆች በወሳኝ ጊዜያት እጆቻቸዉን እንዲታጠቡ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡
ንፁህ የመጠጥ ዉሃ የሚቀርብባቸዉን ሲንኮች ደግሞ ሰማያዊ ቀለም እንዲኖራቸዉ በማድረግ ዉሃዉ እንዳይባክንና ተማሪዎችም ሳይቸገሩ በፈለጉት ጊዜ ዉሃ እንዲያገኙ ማድረግ ችለዋል፡፡
Partner Education in Ethiopia የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከትምህርት ተቋማት ጋር በርካታ ስራዎችን ሰርቷል፡፡ በመሆኑም ድርጅቱ ቀደም ባለዉ ልምዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ያለዉን ጠቀሜታ በስፋት ተረድቷል፡፡ ከዚህ በላይ እጅን በዉሃና በሳሙና በአግባቡና በወሳኝ ጊዜያት በመታጠብ የተለያዩ በሽታዎችን መከላከል የሚያስችል መሆኑን ተማሪዎች ቢገነዘቡ ለወላጆቻቸዉ ብሎም ለህብረተሰቡ በማስተማር ዉጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል በማመን የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትን እንዲያገኙ አድርጓል ፤ ወደፊትም ይቀጥላል።
ይህን ግንዛቤ በማስረፅ እጅን መታጠብ የሁልጊዜም ተግባር እንዲሆንና በህብረተሰቡ ዘንድ እንደባህል እንዲቆጠር ለማድረግ የራሱን አሻራ አስቀምጧል፤ ወደፊትም በሁሉም ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ በሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ስራው ይሰራል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በየአመቱ ህዳር 16 ቀን የሚከበረዉ የእጅ መታጠብ ቀንም እነዚህ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በስፋት ከሰሩባቸዉ ትምህርት ቤቶች ዉስጥ አንዱ በሆነዉ መስከረም 16 ትምህርት ቤት ‘’የእጅ ንፅህናን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በአንድነት እንስራ’’ እና ’’የአይነ ምድር አወጋገድ ስርአትን በማሻሻል የከርሰ ምድር ዉሃ ብክለትን እንከላከል’’ በሚል መሪ ቃል በድምቀት ተከብሯል፡፡
እኛም በዓሉን ለማክበር በሄድንበት ወቅት ተማሪዎች ንፅህናን አመላካች በሆኑ ዩኒፎርሞች ደምቀዉ
ጤናማ ለመሆን
ንፁህ ፅዱ መሆን
እጁን የታጠበ
ንፁህ ፅዱ ሆነ
የዉሃ በሽታ ተቅማጥ እንዳይዘን
እጃችን መታጠብ ሁሌ እያስታወስን በማለት ይዘምራሉ መዝሙሩን አዳምጠን መዝሙሩ አሰተማሪ ብቻ ሳይሆን አነቃቂም ነዉ፡፡ በፈገግታ ተሞልተዉ ከሚያዜሙት ተማሪዎች ጎን አንድ መምህር ተመለከትን መምህር ዘመኑ ዓለም ይባላሉ፡፡ መምህር ዘመነ አለም በመስከረም 16 ትምህርት ቤት የንፅህና ክበብ ተጠሪ ናቸዉ። እሳቸዉም ከልጆቻቸዉ ጉን ሆነዉ አብረዉ ይዘምራሉ፡፡ እየተዘዋወሩ ያስተባብራሉ፡፡ ወደ መምህሩ ጠጋ በማለት የክበባችሁ ስራ ምን ያህል ወደ ህብረተሰቡ ደርሷል? የሚል ጥያቄ አነሳንባቸዉ፡፡ እሳቸዉም በልበ ሙሉነት ህብረተሰቡ በጣም ተጠቃሚ ነዉ፡፡ ልጁን የቀለም ትምህርት ሊያስተምር ላከ፡፡
ልጆቹም ፊደል ከማንበብ ቁጥር ከመደመር ከመፃፍ አልፈዉ ለጤናዉ ዋስትና የሆነ ትምህርት ይዘዉ ወደቤቱ ገቡ ከዚህ በላይ ምን ጥቅም አለ፡፡ በነገራችን ላይ አሉ መምህሩ በነገራችን ላይ ወላጆች ልጆቻቸዉ ያሉትን ነገር ያዳምጣሉ፡፡ ያዳመጡትን ይተገብራሉ፡፡ ለኛም መረጃን ይሰጣሉ፡፡ ይህ ለዉጥ በስፋት በትምህርት ቤታችን ተማሪዎችና ወላጆች ላይ የምናየዉ ተግባር ነዉ፡፡
ሌላዉ ነገር ቀደም ሲል ብዙ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸዉ ያቆራርጡ ነበር ምክንያቱም በግቢያችን ንፅህ የመጠጥ ዉሃ እንደልብ አልነበረም ፣ መጸዳጃቤት ችግር ነበር ፣ ሴት ተማሪዎች በወር አበበ ጊዜ የሻወር አገልግሎት የሚያገኙበት ቦታ አልነበረም፡፡ አሁን እነዚህ ችግሮች ተፈተዋል፡፡ እነዚህ ችግሮች ተፈተዋል ማለት ደግሞ የትምህርት ፍትሀዊነትና የትምህርት ጥራት ተጠበቀ ማለት ነዉ፡፡ ይህ ሁሉ ጥረት የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታትና ጤናማና ብቁ ዜጋ ለማፍራት በመሆኑ ህብረተሰቡ ላይ ደርሰናል ህልማችን ተሳክቷል:: በትምህርት ቤታችን የሚገኙ የክበቡ አባላትም ሆነ ከክበብ አባላት ዉጭ የሚገኙ ተማሪዎችም እጆቻቸዉን በአግባቡ በመታጠብ በሽታን ለመከላከል የራሳቸዉን ድርሽ በአግባቡ ይወጣሉ፡፡
ተማሪ ያብስራ መንግስቴና ህይወት ክንዴ የመስከረም 16 ትምህርት ቤት የንፅህና ክበብ አባላት ናቸዉ ዩኒፎርማቸዉን ለብሰዉ በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ያቅማቸዉን ለማድረግ ወደታች ወደላይ ሲሉ ተመልክተናቸዋል፡፡
ትንሽ ቆይተዉ እጅ ወደሚታጠቡበት ቦታ አመሩ እኛም በርቀት እንከታተላቸዉ ነበርና እጆቻቸዉን ታጠቡ፡፡ ከዚያም የመጠጥ ዉሃ ወደሚገኝበትና በሰማያዊ ቀለም በተሰራዉ ሲንከር አመሩ፡፡
እዉነትም ህፃናትን ማስተማር ቤተሰብን ማስተማር ነዉ ያሰኛል፡፡ ልጆቹ ማንም የሚመለከታቸዉ ባይኖርም እጆቻቸዉን በተማሩት መሰረት በተገቢዉ መንገድ ታጥበዋል፡፡ የመጠጡን ለመጠጥ የእጅ መታጠቢያዉንም ለመታጠብ ተጠቅመዋል፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዉ በአግባቡ መሰራቱን ያመላክታል፡፡
ልጆቹ ታጥበዉ ሲጨርሱ ከክበብ አባላት ዉጭ ያሉ ተማሪዎች እጃቸዉን በአግባቡ እንዲታጠቡ ምን ታደርጋላችሁ? በማለት ጠየቅናቸዉ እነሱም ሁልጊዜም የክበቡ አባላት በተማሪዎች የሰልፍ ስነ ስርአት ወቅት ትምህርት ይሰጣል፡፡ የክበቡ አባላትም ስለ ንፅህና አጠባበቅና ጥቅሙ በመዝሙር መልእክት እናስተላልፋለን፣ አሁን ደግሞ የንፅህና መጠበቂያ ቦታዉ የተመቻቸ በመሆኑ ሁሉም ተማሪ በሚባል መልኩ እጆቻቸዉን በአግባቡ ይታጠባሉ ፡፡ በዚህ ትምህርት ቤት የአይነ ምድር አወጋገድም በአግባቡ ተግባራዊ ይደረጋል ፡፡ ለቤተሰቦቻችንም የእጅ መታጠብ ወሳኝ ጊዜያት የሚባሉትን ማለትም
ምግብ ከማዘጋጀታችን በፊት፣ ምግብ ከመመገባችን በፊት፣ ህጻናትን ከመመገባችን ፣ ከመጸዳጃ ቤት መልስ፣ ህጻናትን ካጸዳዳን በኋላ መሆናቸዉንና እነዚህን የመታጠቢያ ጊዜያት በአግባቡና በዉሃና በሳሙና መታጠብ ከተለያዩ በሽታች የሚከላከል መሆኑን እናስተምራለን፡፡ በዚህም እኛም ሆን ቤተሰቦቻችን ዉጤታማ ሆነናል፡፡
ስለዚህ በሌላ አካባቢ የሚገኙ ሁሉም ተማሪዎች እጆቻቸዉን በወሳኝ ጊዜያት ሁሉ በዉሃና በሳሙና በአግባቡ በመታጠብና ወላጆቻቸዉን በማስረዳት እንደኛ ጤናማ እንዲሆኑ እንመክራለን በማለት መልእክታቸዉን አስተላልፈዋል ፡፡