“ከመንግሥታዊ ተቋማትና ረጅ ድርጅቶች በተጨማሪ ማኅበረሰቡ በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)

===========================================

በክልሉ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የተከሰተውን የሥርዓተ ምግብ ችግር ለመቅረፍ መንግሥት እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ባለፈ ማኅበረሰቡም ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።
ከድርቁ ጋር ተያይዞ በአፋጣኝ ሥርዓተ-ምግብ ዙሪያ ከአጋር አካላት ጋር የውይይት ተካሂዷል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ጸጋ ባለማልማቱ ማኅበረሰቡ በተደጋጋሚ ችግር ውስጥ መውደቁን አንስተዋል። አሁን ላይ በክልሉ በተከሰተው ድርቅ ከሚሊዮን በላይ ዜጎች ለረሃብ መጋለጣቸውን አንስተዋል። ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በእንስሳት ላይም ጉዳት ደርሷል፤ ተማሪዎችም ትምህርታቸውን አቋርጠዋል ብለዋል። ለእናቶች እና ለሕጻናት በቂ ምግብ ማቅረብ አለመቻሉን አንስተዋል። በዚህም ዜጎች እየተሰደዱ መኾኑን ገልጸዋል።
ያጋጠመውን ችግር ለመወጣት መንግሥት ከሚያከናውነው ሥራ ባለፈ መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት እየተሠራ ቢኾንም ከችግሩ ስፋት አኳያ የተሠራው ሥራ በቂ አለመኾኑን ገልጸዋል። በመኾኑም ተቋማት፣ ረጅ ድርጅቶች እና ማኅበረሰቡ ጭምር ችግር ላጋጠማቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። የክልሉ መንግሥትም ድጋፍ ከሚያደርጉ አካላት ጎን መኾኑን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ በክልሉ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ የተከሰተውን የሥርዓተ ምግብ ችግር ለመፍታት ከሚመለከታቸው ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እየሠራ ይገኛል።
የተደረጉት ድጋፎች ከችግሩ ስፋትና በክልሉ ከተከሰተው የሰላም ሁኔታ ጋር ተያይዞ በቂ አለመኾኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ሌሎች ድርጅቶች እና ማኅበረሰቡም ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ኢንስቲትዩቱ በክልሉ ሥርዓተ ምግብ ላይ ምርምር እና የዳሰሳ ጥናት ማካሄዱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በቅርቡም የሥነ ምግብ እና ሥርዓተ ምግብ ቤተ ሙከራ ለማስጀመር እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱል ከሪም መንግሥቱ በአማራ በክልል የተከሰተው ድርቅ ከሥርዓተ ምግብ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን መቀጨጭ እና መቀንጨር አባባሽ ምክንያት መኾኑን ገልዋል። ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ሕጻናት እና እናቶች የተደረገው የአልሚ ምግብ ተደራሽነት ውስንነት እንደነበረውም ገልጸዋል። ችግሩን ለመቅረፍ የሁሉንም ድጋፍ ይጠይቃል ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *