የክልል እና ሀገር ዓቀፍ ፈተና ዝግጅት
ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም
አበባ ጋሻው በባሕር ዳር ከተማ በቁልቋል ሜዳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ናት:: አበባ በመጭው ሰኔ ወር ላይ ለሚሰጠው የሀገር አቀፍ ፈተና ዝግጅት ከሚያደርጉ ተማሪዎች አንዷ ናት::
አበባ እንደነገረችን ትምህርታቸውን በክፍል ውስጥ በአግባቡ ከመማር በተጨማሪ ለሀገር አቀፍ ፈተናው ተዘጋጅቶ የላቀ ውጤት ለማምጣት የሚያግዛቸው መጻሕፍት ጀነራል ሳይንስ እና አማርኛ ለየግላቸው እንዲሁም ሒሳብ፣ ባዮሎጂ እና እንግሊዝኛ ደግሞ በጋራ (ለሁለት) ተሰጥቷቸዋል:: በአሁኑ ወቅት/ሚያዝያ መጀመሪያ ሳምንት/ የሁለተኛውን ወሰነ ትምህርት በማገባደድ ላይ እንደሆኑም አበባ ተናግራለች::
ሁለተኛውን ወሰነ ትምህርት ከተቀመጠለት ጊዜ ቀድመው ካጠናቀቁ ለፈተና ዝግጅት የሚረዷቸውን የቀደሙ የፈተና ጥያቄዎችን (ወርክ ሽት) በመሥራት ራሳቸውን እንዲፈትሹ መምህራኑ እንደሚያግዟቸው ገልፃለች::
ተማሪዎች በግል ከሚያደርጉት ጥናት በተጨማሪ ክፍት ክፍለ ጊዜ ሲገኝ ቤተ መጻሕፍት በመግባት እንደሚያጠኑ አበባ ነግራናለች::
በባሕር ዳር ከተማ የጎርደማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ አማረ ገበየሁ በበኩሉ ዘንድሮ ለሚወስደው የስምንተኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና መምህራን ከትምህርት ቀናት ውጭ /ቅዳሜ እና እሁድ / ክለሳ እንደሚያደርጉላቸው፣ እንደሚያስተምሯቸው እና ጥያቄዎችን እንደሚያሠሯቸው ተናግሯል:: መጽሐፍ ግን ለጋራ በመሆኑ እንደፈለጉ ለማንበብ መቸገራቸውን አማረ ጠቁሟል::
ናሆም ፍሬው በበኩሉ የስድስተኛ ክፍል ትምህርት በአዲሱ ፖሊሲ ከበድ ቢልም መምህራን በሚገባ ተዘጋጅተው ስለሚያስተምሯቸው እና ድጋፍ ስለሚያደርጉላቸው ፍርሃታቸው እንደለቀቃቸው ነው የሚናገረው:: ቅዳሜ እና እሁድ ተጨማሪ ትምህርት እየወሰዱ መሆኑም ለመጀመሪያ ጊዜ ዘንድሮ በሚሰጠው ክልል ዓቀፍ ፈተና ጥሩ ውጤት ለማግኘት እንደሚያግዛቸው ተስፋ ሰንቋል:: ግንቦት 12 የሚሰጠው ሞዴል ፈተናም ለዋናው ፈተና ሊያግዛቸው ስለሚችል በጉጉት በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልፆልናል::
የአፄ ሠርፀድንግል መላዕክ ሰገድ መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ዓባይነህ የሽዋስ እንዳሉን ተማሪዎችን ለማብቃት እና ለመጭው ፈተና ለማዘጋጀት ከመምህራን እና ተማሪዎች ጋር በመግባባት እየተሠራ ነው:: በተለይም የስድስተኛ ክልላዊ ፈተና ለመጀመሪያ ጊዜ ስለሚሰጥ ተማሪዎችን የላቀ ውጤት ባለቤት ለማድረግ እየተሠራ ነው:: ዓመታዊ የትምህርት እቅዱ እንዲሳካም ለመምህራን አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ሁኔታውም የተስተካከለ እንደሆነ ርእሰ መምህሩ ገልፀዋል::
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም እሸቴ እንደገለጹት ተማሪዎች በመደበኛ ክፍለ ጊዜያቸው በአግባቡ እየተማሩ እና በትምህርት ቤቶች መሠራት የሚገባው እንዲከናወን ተደርጓል:: የደረሰው መጽሐፍ ለሁሉም ተማሪ ለማዳረስ በቂ ባይሆንም የመጣውን ግን በአግባቡ ለጋራ ለማከፋፈል ተሞክሯል::
እንደ መምሪያ ኃላፊው ማብራሪያ በሀገር እና ክልል አቀፉ ፈተና እንደ ባሕር ዳር ከተማ ስድስተኛ ክፍል ከ6 ሺህ 500 በላይ እንዲሁም ስምንተኛ ክፍል ከ6 ሺህ በላይ ተማሪዎች በ2016 የትምህርት ዘመን ለፈተና ይቀመጣሉ:: ሀገር አቀፍ ወይም ክልል አቀፍ ፈተና ሲባል የተለየ ነገር እንዳልሆነ በተሰጣቸው አቅጣጫ አተኩረው እንዲሠሩ ግንዛቤ ተፈጥሮላቸዋል:: ቀጣይም የሥነ ልቦና ዝግጅት እንዲያደርጉ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እየተሠራ ሲሆን እስካሁን ላልተሸፈኑ የትምህርት አይነቶች ዝግጅትም በቂ ጊዜ አለ::
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እየሩስ መንግሥቱ የ2016 ትምህርት ዘመን የስምንተኛ ክፍል ሀገር አቀፍ እና የስድስተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና በመጭው ሰኔ ወር በሁለት ዙር ለመስጠት አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አሳውቀዋል::
ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ በመማር ማስተማሩ ሂደት በዓመቱ ሊሠራ በታሠበው የጊዜ ገደብ ያልተጠቀሙ ትምህርት ቤቶች እንደገና የትምህርት ጊዜ መቁጠሪያ/የካላንደር/ ክለሳ ተደርጎ በዓመቱ መጀመሪያ መጀመር ያልቻሉትም እንደገና ማካካሻ አንዲያደርጉ እንደተሠራ ቢሮው ድጋፍ እያደረገ ነው:: በግብዓት አቅርቦት በኩል ደግሞ በክልሉ 44 ሺህ ወንበር ተሠርቶ ለትምህርት ቤቶች ተሰራጭቷል:: በክልል ከታተመው 14 ነጥብ 3 ሚሊየን መጽሐፍ አንደኛ እና ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤትን ጨምሮ አራት ነጥብ ስምንት ሚሊየን መጽሐፍ ተሰራጭቷል:: ለሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ደግሞ አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን መጽሐፍ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ደርሶ ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊየን ተሰራጭቷል:: እንደ ክልል በዓመቱ መጀመሪያ የስምንተኛ ክፍል ፈተና ያስፈትናሉ ከተባሉ 5 ሺህ 806 ትምህርት ቤቶች ምዝገባ ያደረጉት 4 ሺህ 155 ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው::
እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ገለጻ የስድስተኛ እና የስምንተኛ ክፍል ፈተና የሚሰጠው በሁለት ዙር ነው:: ቀድመው የተመዘገቡት ፈተናውን ሰኔ ላይ ሲወስዱ ዘግይተው የተመዘገቡ፣ በመሃል ያቋረጡ፣ መማር ያለባቸውን ክፍለ ጊዜ በአግባቡ ያላጠናቀቁ በሁለተኛው ዙር ይፈተናሉ::
ወ/ሮ እየሩስ እንደገለፁት ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚሰጠው የስድስተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ተማሪዎቹ በተለይም በሥነ ልቦና ዝግጁ ለማድረግ እየተሰራ ነው:: ለስምንተኛም ሆነ ለስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች የሚሰጠው ፈተና ይዘት የሚያጠቃልለው በዘንድሮው ዓመት የተማሩትን ብቻ መሆኑም ተመላክቷል:: በክልሉ አጠቃላይ 133 ሺህ የስድስተኛ እና ከ150 ሺህ በላይ የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናውን ይወስዳሉ::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የም