በክልሉ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እየተካሄደ መኾኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
==========================
በክልሉ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እየተካሄደ መኾኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ውጤታማነት ተጨማሪ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እያደረገ መኾኑ ተመላክቷል፡፡
በአማራ ክልል በሚገኙ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች በተከታታይ ዓመታት በተሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡ ይታወሳል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደግሰው መለሰ የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት የማሥፋፋት እና ደረጃቸውን የማሻሻል ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በሰሜኑ ጦርነት በርካታ ትምህርት ቤቶች መጎዳታቸውንም አንስተዋል፡፡ አሁን ባለው የክልሉ ወቅታዊ ጸጥታ በርካታ ትምህርት ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል ነው ያሉት፡፡
በክልሉ ትምህርት ቤቶችን ለማደስ ጥረት እየተደረገ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡ በትምህርት ቢሮው፣ በአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ጽህፈት ቤት፣ በአማራ ልማት ማኅበር፣ በትምህርት ሚኒስቴር እና በሌሎች አጋር አካላት በርካታ ትምህርት ቤቶችን ለማደስ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችም እየተገነቡ መኾናቸውን አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ መንግሥት ሦስት አዳሪ ትምህርት ቤቶች በሦስት ከተሞች ላይ እየተገነቡ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የአዳሪ ትምህርት ቤቶቹ ሰቆጣ፣ ፍኖተ ሰላም እና ደብረ ታቦር ላይ እየተገነቡ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በየአካባቢዎች የትምህርት ቤቶች እድሳት እና አዳዲስ ግንባታዎች እየተሠሩ እንደሚገኙም አመላክተዋል፡፡
ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እና ጥራት እንዲጠናቀቅ ሁሉም ሰላሙን በማረጋገጥ እና በመደገፍ ውጤታማ እንዲኾኑ ማድረግ ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡ እየተገነቡ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በጥሩ ደረጃ ላይ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
አዳሪ ትምህርት ቤቶች ውጤታማ ናቸው ያሉት ኀላፊው የክልሉ መንግሥት የተምህርት ቤቶችን ውጤታማነት በመገንዘብ ግንባታዎችን እያከሄደ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለማስገንባት እንቅስቃሴ እያደረጉ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
ለአብነት ጎንደር ዪኒቨርሲቲ ከዳሽን ቢራ ፋብሪካ ጋር በጋራ በመኾን የአዳሪ ትምህርት ቤት ለመሥራት የመሠረተ ድንጋይ ማስቀመጣቸውን ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እና ባለሃብቶች ተሞክሮውችን በመውሰድ የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለማስፋፋት እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በአዳሪ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ክልሉም ሀገርም የሚኮራባቸው እየኾኑ መምጣታቸውንም ገልጸዋል፡፡
የተጀመሩ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች እንዲጠናቀቁ እና አዳዲስ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች እንዲገነቡ ተቋማት እና ግለሰቦች ርብርብ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡ በብዙ መልኩ የተገጎዱ ትምህርት ቤቶችን ለማደስም ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን አማራጮች ይጠቀሙ
1. በዌብ ሳይት ገጻችን http://www.anrseb.gov.et/
3. በፌስ ቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau
4. በቴሌግራም ቻናላችን t.me/anrse

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *