በአማራ ክልል በ2017 የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ከ7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱ ይታወሳል።
ይሁን እንጅ እስከ መስከረም 8/2017 ዓ.ም በክልሉ መመዝገብ የተቻለው በ89 በመቶ በሚኾኑ ወረዳዎች፣ 55 በመቶ በሚኾኑ ትምህርት ቤቶች 2 ሚሊዮን 295 ሺህ 150 ተማሪዎችን ብቻ መኾኑን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
በተለይም ደግሞ ከፍተኛ የተማሪ ቁጥር እንዳላቸው በሚታመንባቸው ሰሜን፣ ምዕራብ እና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖች፣ ደቡብ ጎንደር ዞን እና ከፊል አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የተማሪ ምዝገባው ዝቅተኛ መኾኑን አስረድተዋል።
በሰሜን፣ ምዕራብ እና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖች ደግሞ 10 በመቶ እንኳ ምዝገባ ማካሄድ አለመቻሉን አንስተዋል።
በክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በተሟላ መንገድ ወደ ሥራ እንዲገቡ ከማኅበረሰቡ እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሠራ መኾኑን ኀላፊዋ ገልጸዋል።
ዘግይተው ለሚመዘገቡ ተማሪዎች ቢሮው የተለየ አሠራርም እንደሚከተል ተናግረዋል። ይዘቶችን ከጊዜ ጋር መከለስ፣ ቅዳሜ እና እሑድን ጨምሮ ትርፍ ሰዓትን ማስተማር፣ ክፍለ ጊዜ በመጨመር እና ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ሊተገበር እንደሚችል ነው የገለጹት።
ያልተመዘገቡ ተማሪዎች በፍጥነት ተመዝግበው ትምህርት እንዲጀምሩም ሁሉም አካል ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ዘገባው የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን
