በአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የስድስት ወራት የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የትምህርት ሥራዎችን ችግሮች አጽንኦት ሰጥተው ዘርዝረዋል።
“ትምህርት በራሱ ልማት ነው፤ የሁሉም ልማቶች የማሳለጫ መሠረትም ነው” ሲሉ ገልጸዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።
ትምህርት ለተሻለ ነገ ያበቃል፤ በመኾኑም የክልሉ መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሢሠራ ቆይቷል ነው ያሉት።
የክልሉ ሕዝብ ልጆቹን የማስተማር ፍላጎቱ ከፍተኛ ቢኾንም ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ግን የዘርፉ ሳንካ ስለመኾኑ ገልጸዋል።
በግጭት ምክንያት ከተጎዱ ዘርፎች ውስጥ ትምህርት አንዱ ነው፤ የትምህርት ዘርፍ የዕድገት ምጣኔ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ እየቀነሰ መጥቷል ነው ያሉት።
ለአብነትም የ2016 በጀት ዓመት የትምህርት ዘርፍ ዕድገትን አንስተው ዘርፉ እጅግ የተጎዳ እንደኾነ አመላክተዋል።
የዝቅተኛ ዕድገት ምጣኔው መነሻ ክልሉ የገጠመው ተከታታይ ግጭት እና ከዚህ ጋር ተያይዞ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መምጣት አለመቻላቸው እንደኾነም አስገንዝበዋል።
“የትምህርት መቋረጥ የትውልድ ቅብብሎሽን የሚገታ ታላቅ ስብራት ነው፤ ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ በጉልህ መክሮ አቅጣጫ ሊያስቀምጥለት ይገባል” በማለትም ርእሰ መሥተዳድሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ቢኾን የክልሉ መንግሥት በትምህርት ዘርፍ ልዩ ልዩ ተግባራት ሲያከናውን መቆየቱን ጠቅሰዋል። ለአብነትም የትምህርት ግብዓት ማሟላት እና የመማሪያ ክፍሎችን መገንባት እና ማደስ ተጠቅሰዋል።
2 ሺህ 210 አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተዋል፤ 8 ሺህ 882 ክፍሎች ደግሞ ለተማሪዎች በሚመች መልኩ ታድሰዋል ነው ያሉት። 19 ሺህ 645 የሚኾኑ የተማሪ ወንበሮችን ማቅረብ መቻሉንም ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል።
በክልሉ በጀት ከ4 ሚሊዮን 22 ሺህ በላይ አዳዲስ የመማሪያ መጽሐፍት ታትመው 75 በመቶው ስለመሰራጨታቸውም አንስተዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር ደረጃ ደግሞ ከ6 ሚሊዮን 626 ሺህ በላይ መጽሐፍት ታትመው 61 በመቶው ተሠራጭተዋል።
ይህ ሲሰላ በአጠቃላይ ከ10 ሚሊዮን 648 ሺህ በላይ መጽሐፍት ታትመው ለክልሉ ስለመድረሳቸውም አብራርተዋል።
የጸጥታ ችግሩ መጽሐፍትን ለተማሪዎች የማሰራጨት ሂደቱን ጭምር እያወከ እንደሚገኝም ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል።
ይሁን እንጅ መሰናክሎችን በመቋቋም አብዛኛውን መጽሐፍት እና ሌሎችንም የትምህርት ቁሳቁስ ለማሰራጨት ሰፊ ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት።
በጋራ ቆሞ ሰላምን በማረጋገጥ በዕውቀት የተገነባ ትውልድ እና ሀገር መገንባት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።