በክልሉ የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን ማስፋት እንደሚገባ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
ደብረ ማርቆስ: ሰኔ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክቡር ዶክተር ሃዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በክልሉ ከሚገኙ አዳሪ ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ ነው። ይህ ትምህርት ቤት በ2012 ዓ.ም ነበር ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው።
አዳሪ ትምህርት ቤቱ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በመስጠት በክልሉ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡ ይታወሳል።
የ2017 ዓ.ም ተፈታኝ የአዳሪ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች በሀገር አቀፍ ፈተናው ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጂት እያደረጉ መኾኑንም ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ ባለፉት ሁለት ዓመታት በትምህርት ቤቱ የተመዘገበውን ከፍተኛ ውጤት ለማስቀጠል እንደሚተጉም ገልጸዋል። በመምህራን እና የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ በፈተናው ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የተለያየ እገዛ እያደረጉላቸው መኾኑንም ጠቅሰዋል።
የክቡር ዶክተር ሃዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የኬሚስትሪ መምህር ትዕግስቱ ዋሴ ተማሪዎችን ለፈተናው ብቁ ለማድረግ በቡድን እና በግል እንዲያጠኑ ከማድረግ ባሻገር በሥነ ልቦና ዝግጁ እንዲኾኑ እየሠሩ መኾኑንም ገልጸዋል።
የክቡር ዶክተር ሃዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ምክትል ርእሰ መምህር ዘመኑ ምህረቴ ተማሪዎች ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እና ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ብሎም ለፈተናው ዝግጁ እንዲኾኑ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በክልሉ በሚገኙ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች ባለፉት ዓመታት ያስመዘገቡትን ከፍተኛ ውጤት በዚህ ዓመትም በተሻለ መንገድ እንዲደግሙ ልዩ ድጋፍ እየተደረገ ስለመኾኑ ነው ለአሚኮ የገለጸው።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ እየሩስ መንግሥት ባለፉት ሁለት ዓመታት በልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተመዘገቡ ውጤቶች አበረታች ነበሩ ብለዋል። ይህን ውጤት በዚህ ዓመትም በተሻለ መንገድ ለመድገም ልዩ ድጋፍ እየተደረገ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
ምክትል ኀላፊዋ በክልሉ በአዳሪ ትምህርት ቤቶች እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችን ለማስቀጠል ነባር አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በግብዓት ከማጠናከር ባለፈ በፍኖተ ሰላም፣ በደብረ ታቦር እና በሰቆጣ ከተሞች አዳዲስ አዳሪ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ ነው ብለዋል።
የ2017 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ከሰኔ 23/2017 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 8/2017 ዓ.ም እንደሚሰጥ ይታወሳል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *