የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች እየተሰጠ ነው፡፡
***********
ባህርዳር፡ ሰኔ 3/2017ዓ.ም(ትምህርት ቢሮ) የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች እየተሰጠ መሆኑን ተገለጸ፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ.ር)፣ የትምህርት ቢሮ ም/ሃላፊዎች እና የባህርዳር ከተማ ትምህርት መምሪያ ሃላፊ ሙሉዓለም አቤ(ዶ.ር) በባህርዳር ከተማ መስከረም 16 እና ሚሊኒየም አካዳሚ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት ፈተናውን አስጀምረዋል፡፡
የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ሃላፊ ሙሉዓለም አቤ(ዶ.ር) በ2017ዓ.ም እየተሰጠ ያለው የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ፍጹም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ እየተሰጠ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ተከታታይነት ያላቸው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሰራታቸውን ያወሱት ሃላፊው ፈተናው በ49 ትምህርት ቤቶች 7288 ተማሪዎች ፈተናውን እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡ ፈተናው በስኬት እንዲጠናቀቅም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ያለሰለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ጠይቀዋል፡፡
በትምህርት ቤቶች ተገኝተው ፈተናውን ያስጀመሩት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ.ር) የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች እየተሰጠ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ፈተናው በሁለት ዙር የሚሰጥ በመሆኑ በሁለቱም ዙሮች በ2728 ትምህርት ቤቶች 148,169 ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ላይ ይቀመጣሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከሰኔ 3-4/2017 በሚሰጠው የመጀመሪያው ዙር የ8ኛ ክፍል ፈተና 130,280 ተማሪዎች በ2275 ትምህርት ቤቶች ፈተናውን ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ከሰኔ 5-6/2017ዓ.ም የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና እንደሚሰጥ የጠቆሙት ሃላፊዋ በዚህም በመጀመሪያው ዙር 131,993 ተማሪዎች በ3055 ትምህርት ቤቶች ፤ በሁለተኛው ዙር 22,221 ተማሪዎች በ594 ትምህርት ቤቶች ፈተናቸውን እንደሚወስዱ ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ በሁለቱም ዙሮች 154,214 ተማሪዎች በ3649 ትምህርት ቤቶች ፈተና እንደሚሰጥ ነው የተገለጸው፡፡
ተማሪዎች ፈተናውን በጥሩ ውጤት ለማለፍ አመት ሙሉ ሲዘጋጁ የቆዩበት በመሆኑ ሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላትና ማህበረሰቡ ፈተናው በስኬት ተጀምሮ በስኬት እንዲጠናቀቅ ርብርብ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ አመት ሙሉ ሲዘጋጅ የከረመን ተማሪ ፈተና ለማደናቀፍ መሞከር ከሰውነት ተራ መውጣት እኩይ ድርጊት እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር ሙሉነሽ ይህንንም ማህበረሰቡ አጥብቆ ሊያወግዝና ሊኮንን፣ ፊት ለፊት ሊጋፈጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *