የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ከነገ ሰኔ 23 ጀምሮ እስከ ሰኔ 25/2013 ዓ.ም ድረስ ይሰጣል፡፡ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ለተፈታኝ ተማሪዎች መልካም የፈተና ጊዜ ይመኛል፡፡ በፈተና ወቅት የተፈታኝ ተማሪዎች መብትና ግዴታዎች ምን ምን ናቸው? ግዴታዎችን የተላለፈ/ ያላከበረ ተፈታኝ ምን ቅጣት ይጠብቀዋል? ቀጥሎ ባለው ዝርዝር የፈተና ህግ ውስጥ መመልከት ትችላላችሁ፡፡
ምዕራፍ አራት
በፈተና አሰጣጥ የተፈታኞች መብት፣ ግዴታና ቅጣት
አንቀጽ 33፡- የተፈታኞች መብት
1) ማንኛውም ተፈታኝ ስለፈተና አሰጣጡ በሚሰጠው ገለጻ ላይ ተገኝቶ በቂ ግንዛቤ የማግኘት መብት አለው፡፡
2) ፈተናው በሚሰጥበት ጊዜ የተቀደደ ወይም የተበላሸ የፈተና ጥያቄ ጥራዝ ከገጠመው ወይም የተሰጠው የመልስ ወረቀት የተበላሸ ከሆነ ወይም ቢበላሽበት በስርዓት በመጠየቅ ሊያስቀይር ይችላል፡፡
3) ዓይነ ስውር ተፈታኞች ምቹ የመፈተኛ ቦታ የማግኘት፣ የፈተና ጥያቄዎችን የሚያነብላቸውና መልሶችን የሚያጠቁርላቸው ፈታኝ የማግኘት መብት አላቸው፡፡
4) አንድ ተፈታኝ በፈተና ላይ እያለ የጤና መታወክ ወይም ፈተናውን እንዳይሠራ የሚያውኩ ሁኔታዎች ቢገጥሙት ችግሩን ለፈታኙ በመግለፅ እርዳታ ማግኘት ይችላል፡፡ ይሁን እንጅ ለባከነው ጊዜ ተጨማሪ ሰዓት አይፈቀድም፡፡
5) ከመፈተኛ ክፍል ውስጥም ሆነ ውጭ ከማንኛውም ድምጽ፣ እወካና እረብሻ ነጻ ሆኖ በነጻነት ተረጋግቶ በሙሉ የአእምሮ ጥረት ፈተናውን የመስራት መብት አለው፣
6) በጤና ችግር ወይም በወሊድ ምክንያት በፈተና ጣቢያ ተገኝቶ ፈተና መውሰድ ያልቻለ/ያልቻለች/ ተፈታኝ በሚቀጥለው ዓመት ትምህርቱን ተምሮ/ራ ፈተናውን ይፈተናል/ትፈተናለች፡፡
አንቀጽ 34፡- የተፈታኞች ግዴታ
1) ማንኛውም ተፈታኝ ስለፈተና አሰጣጥ የሚሰጠውን ገለፃ መከታተል አለበት፡፡
2) ማንኛውም ተፈታኝ ፈተና በሚሰጥባቸው ቀናት ፈተናው ከሚጀመርበት ጊዜ አንድ ሰዓት ቀደም ብሎ በፈተና ጣቢያ መገኘት ይኖርበታል፡፡
3) ማንኛውም ተፈታኝ ወደ ፈተና ክፍል ለመግባት የፈተና መግቢያ ካርድ ይዞ መገኘት አለበት፡፡
4) ሞባይል፣ ካልኩሌተርና ሌሎች ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ወደ ፈተና አዳራሽ ይዞ መግባት ክልክል ነው፡፡ በፈተና ክፍል ውስጥ ማስቲካ ማኘክና ሌሎች ድምጽና ሽታ የሚፈጥሩ ነገሮችን መጠቀም አይቻልም፡፡
5) ማንኛውም ተፈታኝ በፈተና ወቅት የት/ቤቱን የደንብ ልብስ ማክበር ይኖርበታል፡፡ በጤና ችግር ወይም ሃይማኖታዊ አለባበስ ካልሆነ በስተቀር ቆብ፣ ሻሽ፣ መነጸር፣ ኮፍያ በፈተና አዳራሾች መጠቀም አይቻልም፡፡
6) ተፈታኞች ለፈተና አገልግሎት የሚውሉ እንደ እርሳስ፣ ላፒስና መቅረጫ ያሉ ቁሳቁሶችን ይዘው መገኘት አለባቸው፤ መወዋስ አይፈቀደም፡፡
7) ተፈታኞች በተደለደሉበት የመፈተኛ ክፍልና ፈታኞች በፈቀዱላቸው በቀመጫ ወንበር ተጠቅመው መፈተን ይኖርባቸዋል፡፡
😎 የፈተና ጥያቄዎችን መስራት ከመጀመሩ በፊት በፈተና መልስ ወረቀት ላይ የግል መለያ መረጃዎቹን በሙሉ ግልጽ በሆነ ሁኔታ መጻፍ ይኖርበታል፡፡
9) ፈተናው ከተጀመረ ከ20 ደቂቃ በኋላ ወደ ፈተና ክፍል መግባት የተከለከለ ሲሆን ፈተናው ተጀምሮ 30 ደቂቃ ካልሞላ ፈተናውን ሠርቶ ቢያጠናቅቅም እንዲወጣ አይፈቀድለትም፡፡
10) ከላይ በንዑስ አንቀጽ “3” የተገለፀው እንደተጠበቀ ሆኖ ፈተናው ከመጠናቀቁ በፊት ከፈተና ክፍል ለመውጣት የፈለገ ተፈታኝ የጥያቄ ጥራዝና የመልስ ወረቀቱን ለፈታኙ አስረክቦ መውጣት ይችላል፡፡ ሆኖም ፈተናው ሊጠናቀቅ ከ10 ደቂቃ ያነሰ ጊዜ ሲቀረው ማንኛውም ተፈታኝ የተፈቀደው የጊዜ ገደብ እስኪያበቃ በቦታው መቆየት ይኖርበታል፡፡
11) ተፈታኞች የተመዘገቧቸውን ሁሉንም የትም/ዓይነቶች የመፈተን ግዴታ አለባቸው፡፡ አንዱን ካልተፈተኑ በሌሎች ትምህርቶች የተገኙት ውጤቶች አይያዙም፡፡
12) ማንኛውም ተፈታኝ የፈተና አሰጣጥ ደንቦችን ማክበር ይጠበቅበታል፡፡ የፈተና አሰጣጥ ደንብ በመተላለፉ ለሚደርስበት ቅጣት ኃላፊነቱን ይወስዳል፡፡
አንቀጽ 35፡- የፈተና ደንብ የተላለፉ ተፈታኞች ቅጣት
1) በፈተና አሰጣጥ ወቅት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ጥፋቶች የፈፀመ ተፈታኝ የተፈተናቸውን ወይም የሚፈተናቸውን ፈተናዎች ውጤት ሙሉ በሙሉ ይሰረዝበታል፣
ሀ. በስሙና በተሰጠው የምዝገባ ቁጥር ሌላ ሰው ያስፈተነ፣
ለ. በሌላ ሰው ስምና ምዝገባ ቁጥር የተፈተነ፣
ሐ. ከራሱ ፈተና ውጪ ለሌላ ተፈታኝ መልስ የሠራ፣
መ. ፈታኝን የሰደበ፣ የዛተና የደበደበ/ለመደብደብ የሞከረ/፣
ሠ. የሌላን ተፈታኝ የፈተና ወረቀት ወይም የመልስ ወረቀት የቀማ ወይም ለመቀማት የሞከረ፣
ረ. በፈተና ክፍል ውስጥ ሌላውን ተፈታኝ ተረጋግቶ ፈተናውን እንዳይሰራ ያወከና ማናቸውንም ዓይነት የኃይል ወይም የጉልበት ተግባር በሌላ ተፈታኝ ላይ የፈፀመ፣
ሰ. የፈተና ጥያቄ ወረቀቱን በፈተና ሂደት ወቅት ከፈተና ክፍል ውጭ እንዲወጣ ለማድረግ የሞከረ ወይም ያወጣ፣
ሸ. ሌሎች ተፈታኞችን በማሣደም የፈተና ክፍሉንም ሆነ የፈተና ጣቢያውን ሰላም በማወክ የፈተናውን ሂደት ለማስተጓጎል የሞከረ፣
ቀ. በፈተና ክፍል ውስጥ ሞባይል ይዞ የተገኘ፣
ተ. በፈታኙ የሚሰጠውን ምክርና ተግሳፅ ባለመቀበል በአንድ የፈተና ክፍለ ጊዜ ተደጋጋሚ ጥፋቶች የፈፀመ፣
ቸ. ከላይ ከተዘረዘሩት ጥፋቶች እኩል/አቻ የሚሆኑ ሌሎች ጥፋቶችን የፈፀመ፣
ነ. ለሌላ ሰው ሲፈተን የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ በህግ አግባብ የሚጠየቅ ከመሆኑ በተጨማሪ በየትኛውም የትምህርት ደረጃ በመማር ላይ ከሆነ ለአንድ ዓመት ከትምህርቱ ይታገዳል፡፡
2/ በፈተና አሰጣጥ ወቅት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ተግባራት የፈፀመ ተፈታኝ ጥፋት የፈጸመባቸው የፈተና አይነት ውጤት ብቻ ይሰረዝበታል፡
ሀ. ሁለት ወይም ከሁለት በላይ ሆነው ፈተናውን በጋራ መስራት፣
ለ. ሆነ ብሎ የፈተና መልስ ሲያስቀዳ/ ሲነጋገር ወይም በወረቀት ጽፎ ለሌላ ተፈታኝ ያስተላፈ ወይም የተቀበለ፣ የሠራበትን የፈተና ጥያቄ ወረቀት ለሌላ ሰው ሲሰጥ ወይም ሲቀበል የተገኘ፣
ሐ. አጫጭር ማስታወሻዎች በወረቀት ወይም በሌላ መልክ ይዞ በፈተና አዳራሽ ውስጥ የተገኘ፣
መ. ከውጭ ተሰርቶ የገባ መልስ ተጠቅሞ ፈተናውን የሠራ፤
ሠ. በአንድ የትምህርት ዓይነት ፈተና ሁለት የመልስ ወረቀቶች በአንድ ተፈታኝ ስምና የምዝገባ ቁጥር ተሠርቶ ከተገኘ፣
ረ. የፈተና መልስ መስጫ ወረቀቱን ሆን ብሎ ያበላሸ፣ የቀደደ፣
ሰ. ተፈታኞች ወደ ፈተና አዳራሽ ይዘው መግባት ከተፈቀደላቸው የትምህርት መሣሪያዎች ውጭ ይዞ የገባ፣
ሸ. ከላይ ከተዘረዘሩት ጥፋቶች አቻ/እኩል የሆኑ ሌሎች ጥፋቶችን የፈፀመ፣
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ Amhara National Regional State Education Bureau
በዌብሳይት https://www.anrseb.gov.et/bahirdar/
በቴሌግራም https://t.me/anrse
ፌስቡክ https: Amhara Education Bureau
Amhara National Regional State Education Bureau (https://www.anrseb.gov.et/)
Amhara National Regional State Education Bureau – Quality Education for All
anrseb.gov.et, Amhara National Regional State Education Bureau, Amhara Education Bureau, Bahirdar,East Gojjam, Weste