ከአሸባሪው የህወሃት ቡድን ነጻ በወጡ አካባቢዎች ሲያስተምሩ የነበሩ መምህራን ህብረተሰቡን በማረጋጋት የመማር ማስተማር ሂደቱን እንዲያስጀምሩ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ጥሪ አቀረበ፡፡
——————————————————————————————————–
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከተባበሩት መንግስታት ህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ጋር በመተባበር አሸባሪው ቡድን ወረራ ባካሄደባቸው የሰ/ወሎ፣ዋግ ኽምራና ሰ/ጎንደር ዞኖች ለሚያስተምሩ መምህራንና የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች የስነ ልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ ስልጠና በደብረታቦርና እንጅባራ ከተሞች በሁለት ዙር 2ሺህ ለሚሆኑ መምህራን እየተሰጠ ነው ፡፡
በደብረታቦር የስልጠና ማእከል ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ማተብ ታፈረ /ዶክተር/ አሸባሪውና ወራሪው የህወሃት ቡድን የትምህርት ተቋሞቻችን ላይ ከፍተኛ የሆነ ውድመትና ጉዳት ማድረሱን ገልጸው ነጻ በወጡ አካባቢዎች መምህራን ወደ ትምህርት ቤቶቻቸው ሲመለሱ የትምህርት ቤታቸውን የጉዳት መጠን በመመዝገብ ለታሪክ ሊያስቀምጡ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
ኃላፊው መምህራን በህብረተሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተደማጭነት በመጠቀም ህብረተሰቡ በደረሰበት መራር ግፍና በደል ምክንያት ከገባበት የስነ ልቦና ጫና በማውጣት የማረጋጋት ስራ እንዲሰሩና የመማር ማስተማር ስራ እንዲያስጀምሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በእንጅባራ ስልጠና ማዕከል የተገኙት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ሙላው አበበ ስልጠናውን ለመምህራን መስጠት ያስፈለገው መምህራን ከተማሪዎችና ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት የሚገናኙ በመሆናቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አሸባሪው ቡድን የህብረተሰቡን ስነ ልቦና በመጉዳት የተማረና ውጤታማ ትውልድ እንዳይፈጠር አልሞ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው መምህራንም ሴራውን በመረዳት ከምንጊዜውም በላይ ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው በመስራት የዜግነት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከአሸባሪው ቡድን ነፃ በወጡ አካባቢዎች አዲስ የትምህርት ካሌንደር የሚዘጋጅ ሲሆን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ላልወሰዱ ተማሪዎችም ተለዋጭ ፈተና ጊዜ እንደሚዘጋጅላቸው ተመላክቷል፡፡
በባርዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ስነ ባህሪ ፋክሊቲ ዲን ታደሰ መለሰ /ዶክተር/ በበኩላቸው አሸባሪው ቡድን ያደረሰውን የስነ ልቦና ጫና ግንባር ተዋጊዎች መምህራን በመሆናችን በመጀመሪያ መረጋጋትና የአሸባሪውን ቡድን እኩይ ዓላማ በውል መረዳት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የጠፋው የሰው ህይወት፣ ሀብት ንብረት ጉዳቱ የከፋ ነው፡፡ ነገር ግን ህብረተሰቡ ሌላ ዳግም ሞት እንዳይሞት አሁን በጠንካራ ስነልቦና በጋራ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የስልጠናው ተሰታፊ መምህራን በበኩላቸው ስልጠናው በዘርፉ ምሁራን መዘጋጀቱ አሸባሪው ቡድን ከፈጠረባቸው የስነ ልቦና ጫና በመውጣት ወደፊት እንዲያስቡና ተማሪዎቻችንና መላውን ህብረተሰብ ለመታደግ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፡፡ መምህራኑ በቀጣይ ሙሉ አቅማቸው በመጠቀም ህብረተሰቡን በማረጋጋትና በተገኘው ቁሳቁስ ሁሉ ተጠቅመው የመማር ማስተማር ስራውን ለማስጀመር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
የስልጠናውን ዶክመንት በማዘጋጀትና በማሰልጠን የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ፣የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ፣ የመምህራን ትምህርት ኮሌጆችና የቢሮው ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል፡፡
ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያና ዌብ ሳይት አማራጮች ለማግኘት ቀጣዮቹን ሊንኮች ይጠቀሙ ::
ፌስቡክ https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau
ዩቱዩብ https://www.youtube.com/channel/UCARNQWN5bm5z2JmKsC_Cn8w
በዌብሳይት https://www.anrseb.gov.et/
በቴሌግራም https://t.me/anrse