Education planning monitoring & evaluation

 1. ዳራ

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከተቋቋመበት ከ1985 ዓ/ም ጀምሮ የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት የተለያዩ ስያሜዎች ተሰጥተውት የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ  እና ሌሎችንም ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል።  በዚህ መሠረት የመጀመሪያው መዋቅራዊ አደረጃጀት (ከየካቲት 1985 ዓ/ም እስከ ጥር 1989) ድረስ በነበሩት አራት ዓመታት ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን የሥራ ክፍሎ መጠሪያ የፕላንና ፕሮጀክት አገልግሎት የሚል ነበር፡፡  በመቀጠልም ሁለተኛው መዋቅራዊ አደረጃጀት (ከየካቲት 1989 ዓ/ም እስከ መጋቢት 1994 ዓ/ም) ድረስ ባሉት ስድስት ዓመታት ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን የሥራ ክፍሉ መጠሪያም የፕላንና ምህንድስና አገልግሎት የሚል ነበር፡፡ ከዚያም ሦስተኛው መዋቅራዊ አደረጃጀት (ከሚያዝያ 1994 ዓ/ም እስከ ጳጉሜ 1999 ዓ/ም) ባሉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን የሥራ ክፍሉ መጠሪያም የፕላንና ኢንፎርሜሽን አገልግሎት የሚል ነበር፡፡ አራተኛው የትምህርት ዘርፍ መዋቅራዊ አደረጃጀት (ከመስከረም 2000 ዓ/ም እስከ ጥቅምት 2001 ዓ/ም)  ባሉት አንድ ዓመት ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን የሥራ ክፍሉም መጠሪያ የፕላንና ኢንፎርሜሽን አገልግሎት የሚል ነበር፡፡ አምስተኛው የትምህርት ዘርፍ መዋቅራዊ አደረጃጀት (ከህዳር 2001 ዓ/ም እስከ አሁን ድረስ)  ባሉት አስራ ሁለት ዓመታት ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን የሥራ ክፍሉ መጠሪያም በመጀመሪያ አካባቢ የትምህርት መረጃ ስርዓት፣ የዕቅድ ዝግጅት፣ ሐብት ማፈላለግ/ማመንጨት የሥራ አመራር ደጋፊ የሥራ ሂደት ሲሆን ብዙም ሣይቆይ የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት በሚል ስያሜ በአዲስ መልክ እንዲደራጅ ተደርጓል፡፡

 1. የዳይሬክቶሬቱ ተልእኮ

በትምህርት ፖሊሲው ላይ በመመስረት ጥራት ያለውና የህብረተሰቡን ፍላጎት የሚያንፀባርቁ የትምህርት ልማት መረጃ እና የትምህርት ልማት ዕቅድ በማዘጋጀት እና የታቀደውን ዕቅድ በአግባቡ እንዲተገበር ሀብት በማፈላለና/በማመንጨት የትምህርት በጀትን ከፍ በማድረግ የትምህርት ስርዓቱንና ሂደቱን በመደገፍ የትምህርት ግብአቶችን እንዲውሉ የክትትልና ድጋፍ ስርዓት በተጠናከረ መልኩ እንዲከናወን በማድረግ ውጤታማ የሚሆን ሰብአዊ ሀብት ማፍራት ነው፡፡

 1. ዓላማዎች

የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዋና ዓላማ በዓመት ከ200 ሚሊየን ብር በላይ በጀት በሚያንቀሳቅሱ ተቋማት የመሥሪያ ቤቱን እቅድና በጀት እንዲዘጋጅ በማድረግና የእቅድ አፈጻጸምና በጀት አጠቃቀም የሚያሻሽሉ ጥናታዊ ሥራዎችን በመምራት፣ በማስተባበርና እንደ አግባብነቱ ሥራ ላይ እንዲውል በማድረግ፣ የመሥሪያ ቤቱን እቅድና በጀት አፈጻጸም ውጤታማ እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡

 1. ተግባርና ሃላፊነቶች

የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት የሚከተሉት ዋና ዋና ተግባርና ሃላፊነቶች ይኖሩታል፡፡

 • ለፖሊሲ ቀረፃ፣ ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ለዕቅድ ዝግጅት የሚሆኑ ልዩ ልዩ ወቅታዊና ተዓማኒ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በማደራጀትና በመተንተን ዓመታዊ የትምህርት ስታትስቲካዊ መጽሄት ማዘጋጀት፣ እንዲታተምና እንዲሠራጭ ማድረግ፡፡
 • የክልሉ ትምህርት ዘርፍ የረጅም፣ የመካከለኛና የአጭር ጊዜ መሪ እቅድ ማዘጋጀት፡፡
 • የክልሉ ትምህርት ቢሮና ለቢሮው ተጠሪ የሆኑትን 28 ተቋማት የመደበኛ በጀት እቅድ ማዘጋጀት፡፡
 • የመንግሥት፣ የሁለትዩሽ መንግስታትና የበየነ መንግስታት ፕሮጀክት እቅድ ዝግጅት በጥራት እንዲዘጋጅ ማድረግ፣ ማስፀደቅና ማሠራጨት፡፡
 • የትምህርት ዘርፍን እቅድና በጀት አፈጻጸም ክትትልና ሙያዊ ድጋፍ መስጠት፡፡
 • የአጋርነትና የሐብት ማፈላለግ ሥራዎችን በመፈፀም ተጨማሪ ሐብት ማመንጨት፡፡
 1. አደረጃጀት

የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ውስጥ ከሚገኙት የሥራ ክፍሎች መካከል አንዱ ሲሆን የሥራ ክፍሉ በአንድ ዳይሬክተር የሚመራ ሲሆን በስሩም የተመደቡ 9 ባለሙያዎች (ሁለት የስታትስቲካል ዳታ ስርዓት አስተዳደርና ትንተና ባለሙያዎች፣ አንድ የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ባለሙያ፣ ሁለት የፕሮጀክት ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ባለሙያ፣ አንድ የበጀት ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ባለሙያ እና አንድ የአጋርነትና ሀብት ማፈላለግ ባለሙያ) እና ሁለት የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች (ሁለት የቢሮ አስተዳደር እና ኮሚኒኬሽን ባለሙያዎች) አሉት። በዚህ አደረጃጀት የተሰጠውን ተልዕኮ እየተወጣ  ይገኛል።

 1. የሚሰጣቸው ዋና ዋና አገልግሎቶች

የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ከተሰጡት ተግባርና ሃላፊነቶች አኳያ ለደንበኞች የሚሰጣቸው አገልግሎት የሚከተሉት ናቸው፡፡

 • ልዩ ልዩ የትምህርት ስታትስቲካዊ መረጃዎችን ለሚጠይቁ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች መረጃ መስጠት፣
 • በትምህርት ዘርፍ የተዘጋጀውን ዕቅድ እና የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርቶች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ማሠራጨት፣
 • የቢሮውና ለቢሮው ተጠሪ የሆኑ ተቋማት አስመልክቶ የበጀት ዕቅድ ማዘጋጀት፣ የፀደቀውን በጀት መደልደል፣ አፈፃፀሙን መከታተልና የበጀት ዝውውር ማድረግ፣ የበጀት አፈፃፀም ሪፖርት በማዘጋጀት ለዳይሬክቶሬቶች ግብረ መልስ መስጠት፣
 • የካፒታል ፕሮጀክቶች ዕቅድ ማዘጋጀት፣ የፀደቀውን በጀት ማሣወቅ፣ አፈፃፀሙን መከታተልና የፊዚካል እና የፋይናንስ አፈፃፀም ሪፖርት በማዘጋጀት ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሁሉ ግብረ መልስ መስጠት፣
 • በበጎ አድራጎትና ማህበራት ድርጅቶች በኩል የሚቀርቡ የፕሮጀክት ፕሮፖዛሎትን ገምግሞ አስተያየት መስጠት፣ ተቀባይነት ያገኘውን የመያድ ሠነድ በማጋገጥ የውል ስምምነት በመፈራረም ወደ ስራ ማስገባት፣ እንዲሁም ተጨማሪ ሐብት ማፈላለግ/ ማመንጨት ስራ ማከናወን፣