Teachers & School Leaders License & Relicenses

የመምህራን የሙያ ፈቃድ አሰጣጥና ዕድሳት

በ1986ቱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ(ገጽ 20) በግልጽ እንደተቀመጠው መምህራን በሙያቸው ሙሉ ፍላጎት፣ ትጋት፣ የተሻለ ችሎታና ተገቢ የሆነ አካላዊና አእምሮአዊ ዝግጁነት ያላቸው መሆን ይጠበቅባቸዋል። ፖሊሲው በተለይ ለመሰረታዊ ዕውቀት፣ ለሙያዊ ሥነ-ምግባር፣ ለመማር ማስተማር ስልትና ለተግባራዊ  ስልጠና የበለጠ ትኩረት ሰጥቷል። በዚህ መሰረት መምህራን በሙያው ከመሰማራታቸው በፊት በማስተማር ሙያ ለደረጃው የሚመጥን ስልጠናና ትምህርቱን በሚያስተላልፉበት ቋንቋ ብቃት ያላቸው መሆናቸው ይረጋገጣል። እንደሚታወቀው የአገራችን ትምህርት ጥራቱን የሚፈታተኑ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያሉበት እንደመሆኑ መጠን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት መንግስት ለጉዳዩ ቅድሚያ በመስጠት  በየደረጃው የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፎ ለትምህርት ጥራት ማሻሻያ የሚያገለግሉ ማዕቀፎችን  በማዘጋጀት ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

የመምህራን የሙያ ፈቃድ አሰጣጥና ዕድሳት ስርዓት እንደሚዘረጋና መምህራንም በዚህ ስርዓት ማለፍ እንዳለባቸው በአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ማዕቀፍ (2000፣ ገጽ.65) ተገልጿል። በዚሁ መሰረት የመምህራንን የብቃት ደረጃዎች በማሻሻልና ማበረታቻዎችን በመስጠት የመፈጸም አቅማቸውና ክህሎታቸው ከፍ እንዲል ይደረጋል። ይህን ግብ ለማሳካት የተግባር አመላካቾችን በማስቀመጥ  በተለያዩ ደረጃዎች የበቁና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ መምህራንን በማፍራትና የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ትምህርቱን ውጤታማ ማድረግ ያስፈልጋል።

ለዚህም ሲባል የትምህርት ጥራትን በማሻሻል የተማሪዎችን የመማር ውጤት ከማሳደግ አኳያ የተለያዩ አለም አቀፍና (የአውስትራሊያ፣ የኦሀዮና የኒውጀርሲ ሞዳሊቲዎችን) አገር አቀፍ ተሞክሮዎችን በመዳሰስ  ይህ የመምህራን የሙያ ብቃት ደረጃ ተዘጋጅቷል። ደረጃውም ሙያዊ ዕውቀትን፣ ሙያዊ ክንውንንና ሙያዊ ተሳትፎን አካቶ ይዟል።

 አስፈላጊነት

መምህራን የተለያዩ ተማሪዎችን የመማር ፍላጎቶች ለማስተናገድ እንዲችሉ በሚያስተምሩት ትምህርት የይዘትና የተለያዩ የማስተማር ስነ ዘዴ ላይ የተሟላ ዕውቀት ሊኖራቸው ይገባል። ይሁን እንጂ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ መምህራን በተለይ በማስተማር ስልትና ክህሎት ከፍተኛ ክፍተት ያለባቸው መሆኑን የተለያዩ ጥናቶች አመላክተዋል። ለአብነት ያህልም የእንግሊዝኛ ቋንቋ የፋይዳ ጥናት (ሉንድ ዩኒቨርስቲ 2005 እ.ኤ.አ እና ሃረማያ ዩኒቨርሲቲ 2007 ዓ.ም)፣ አገር አቀፍ የ8ኛ ክፍል  የትምህርት ቅበላ ጥናት (2001)፣ የሳይንስና የሂሳብ ትምህርት ማበልጸጊያ ጥናት (SMASEE ,2011) ይጠቀሳሉ። በተለይም የሳይንስና የሂሳብ ትምህርት ማበልጸጊያ ጥናቱ መምህራኑ የቡድን ውይይቶችን፣ የጥያቄና መልስ ተግባራትን የመግለጽና የማሳየት ክህሎትን፣ ውጤታማ የሆኑ የትምህርት ዕቅድ ዝግጅት  የማከናወን እንዲሁም የሚያስተምሩትን ትምህርት ይዘት በተፈለገው የብቃት ደረጃ ጠንቅቆ የማወቅ ክፍተት ያለባቸው መሆኑን አሳይቷል። በተመሳሳይ ሁኔታ በ2000 ዓ.ም የተካሄደው አገር አቀፍ የ8ኛ ክፍል የትምህርት ቅበላ ምዘና የተማሪዎች ውጤት ከሚጠበቀው ደረጃ በታች መሆኑን በግልጽ አሳይቷል። በተጨማሪም በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ የመስክ የክትትል ሪፖርቶችም በአጠቃላይ የተማሪዎች ውጤት  ከዚህ  ችግር የራቁ አለመሆኑን አሳይተዋል።

እነዚህን  ችግሮች በመገንዘብ ትምህርት ሚኒስቴር ይህን የመምህራን ሙያ ብቃት ደረጃ ያዘጋጀ ሲሆን የሙያ ብቃት ደረጃው መዘጋጀት መምህራን፡-

  • ጥራትን መሰረት ያደረገ የመማር ማስተማር ተግባራትን በማከናወንና በዚህ ሂደት ተገቢውን የሙያ ፈቃድ በማግኘትና በማሳደስ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ኃላፊነትና ተጠያቂነትን  መወጣት እንዲችሉ ለማድረግ፣
  • የሙያዊ ዕድገትና የዕድገት ሂደቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለመምራትና ለመደገፍ፣
  • በእያንዳንዱ የስራ ዕድገት ደረጃቸው የሚያደርጉትን የመሻሻልና የዕድገት ክንውኖች በመለየት ተገቢውን ዕገዛ ለማድረግ፣
  • ለስልጠና ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ በማድረግ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማበረታታት፣
  • የግል ሙያዊ ዕውቀታቸውን፣ ሙያዊ ችሎታቸውና ሙያዊ ተሣትፏቸውን ተጠቅመው የሚያከናውኗቸው ተግባራት ስልቶች ከተቀመጡት ደረጃዎች ጋር የተገናዘቡ እንዲሆኑ ለማገዝ፣
  • ለሙያቸው ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳዩ፣ በዚህም ሂደት የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት እንዲያነሳሱና እንዲያሰርጹ ለማስቻል፣

በአጠቃላይ መምህራን ተማሪዎችን ለተሳካና ውጤታማ ለሆነ ህይወት የማዘጋጀት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ነው።

ትክክለኛው የመማር ማስተማር ስራ የሚከናወነው በትምህርት ቤት በመሆኑ ለደረጃው የሰለጠኑና ተነሳሽነት ያላቸው መምህራን አስፈላጊነት አጠያያቂ አይደለም። በትምህርት ቤት ውስጥ በተማሪዎች የትምህርት ውጤት ላይ የሚያሳድረው የተነሳሽነት መንፈስ ወሳኝ ድርሻ አለው። ውጤታማ መምህራን  በትምህርት፣ በስራና በህይወት ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ሁኔታዎች መካከል መምህራን  ለደረጃው ብቃት ያላቸው ሆነው መገኘት በተማሪዎች ላይ የሚፈጥሯቸው አማራጮች የተነሳሽነት ምንጭ ከመሆናቸውም ባሻገር ተማሪዎች በቀላሉ ሊቀበሏቸውና ያገኟቸውን በጎ ተጽዕኖዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ ጥቅም ላይ ሊያውሏቸው ይችላሉ፡፡ መምህራን ወደ ሙያው እንዲገቡ ለመሳብ፣ እድገታቸውን ለማስጠበቅ፣ ተገቢውን ዕውቅና በመስጠት ጥራትና ብቃት ያላቸው መምህራን  በሙያው እንዲቆዩ ለማድረግ በአለም አቀፍም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ አገሮች ለትምህርት ስርዓታቸው የሙያ ብቃት ደረጃ በማዘጋጀት ስራ ላይ እያዋሉት ይገኛሉ። የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አንጻር አለም አቀፍና አካባቢያዊ ጭብጦችን መሰረት በማድረግ የሙያ ብቃት ደረጃ ማዘጋጀትና መተግበር  መምህራን በሙያቸው ያላቸውን ክንውንና ተሳትፎ በአግባቡ ለመምራት ያስችላቸዋል።

ይህም የመምህራንን ሙያዊ ጥራትና ብቃት ለማጎልበት ከማገዙም በላይ ህብረተሰቡ ለሙያው አዎንታዊ  የሆነ ግንዛቤ እንዲኖረው ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ይህ የሙያ ብቃት ደረጃ ማዕቀፍ መምህራን  ተማሪዎቻቸው ስኬታማ እንዲሆኑ አቅጣጫ በመስጠት ህብረተሰቡ በትምህርት ቤቶች የትምህርት አሰጣጥ ስርዓት ላይ ያለው ዕምነት እንዲጨምር ዋና መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል። በተጨማሪም መምህራን በስራ ዘመናቸው በሙሉ ቀጣይነት ባለው የመማር ተግባር በመሳተፍ ሙያቸውን ማጎልበት ያለባቸው መሆኑን የሙያ ብቃት ደረጃው አጽንኦት ይሰጣል።

 የመምህራን የሙያ ብቃት ደረጃ ዓላማ

የመምህራን የሙያ ብቃት ደረጃ ዋና ዓላማ በአገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ጥራት እንዲሻሻል  በሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ ማድረግ ሲሆን  በተጨማሪም የሙያ  ብቃት ደረጃው፡-

  • የተማሪዎችን የመማር ውጤት ለማሻሻል የሚያስችሉ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የማስተማር ስልቶችን ስራ ላይ በማዋል ለትምህርት ጥራት አግባብነት ያላቸውን ተግባራት በማስቀመጥ  የመምህራንን  ተግባርና ኃላፊነት ግልጽ ለማድረግ፣
  • ለስራቸውና ለሙያቸው በሁሉም ደረጃ አስፈላጊውን ዕውቀት፣ ክንውንና ሙያዊ ተሳትፎ ግልጽ የሚያደርግ ማዕቀፍ እንዲኖር ለማስቻል፣
  • መምህራን ከመምህራን፣ ከትምህርት ባለሙያዎች፣ ከትምህርት አመራሮች፣ ከሙያ ማህበራትና ከህብረተሰቡ ጋር ሊኖራቸው የሚገባውን የጋራ ግንዛቤና መግባባት ለማሳየት፣
  • ሙያዊ የትምህርት ግቦችን አዘጋጅቶ ለማሳወቅ፣
  • መምህራን የራሳቸውን የመማር ስኬት የሚገመግሙበት እና ግለ-ጽብረቃና ግለ-ግምገማ የሚያከናውኑበት ማዕቀፍ ለማቅረብ፣
  • መምህራን ላላቸው ሙያዊ ዕውቀት፣ ሙያዊ ክንውንና ሙያዊ ተሳትፎ በራስ መተማመንን ማዳበር እንዲችሉ እውቅና እየተሰጣቸው መሆኑን ለማረጋገጥ፣
  • የሙያውን ክብር ማሳደግ የሚያስችሉ አስተዋጽኦዎችን ለማድረግ፣
  • ሙያዊ ተጠያቂነት እንዲዳብር መሰረት ለመጣል፣
  • መምህራን ተገቢውን ሙያዊ ዕውቀት፣ ሙያዊ ክንውንና ሙያዊ ተሳትፎ በየደረጃው መግለጽ መቻላቸውን እንዲያረጋግጡ ለማገዝ፣
  • የመምህራንን የማስተማር የብቃት ደረጃ ከፍ ለማድረግ፣
  • መምህራን ያለባቸውን የሙያዊ ዕውቀትና ክህሎት ክፍተቶች ለማጥበብ፣
  • የመምህራን ትምህርት ተቋማት ይህን የሙያ ብቃት ደረጃ መሰረት ያደረጉ የስልጠ፣ የስርዓተ- ትምህርትና የዝርዝር ኮርሶች ቀረጻ እንዲያከናውኑ እገዛ ለማድረግ፣
  • መምህራን የተሻለ የመፈጸም ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ለማበረታታት፣
  • የሙያ ብቃት ምዘና ስርዓት በመዘርጋት መምህራን የሙያ ፈቃድ እንዲያገኙ እገዛ ለማድረግ ያስችላል፡፡.