ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በአል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ ።

እንደ ሀገር በስነምግባሩ ምስጉን፣ ስራ ፈጣሪ ፣ቴክኖሎጅ አፍላቂ እና ተጠቃሚ፣ ሀገር በቀል እውቀትን ወደ ላቀ ከፍታ የሚያሳድግ ዜጋን ለማፍራት አቅደን እየሰራን እንገኛለን።

በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚታሰበው ያሳለፍነው ሳምንት ሰሞነ ህማማት የመከራ፣ የሕማም እና የጨለማ ሳምንት እንደኾነ በመታሰብ አልፏል። እየሱስ ክርስቶስ እኛን የሰው ልጆችን ከመከራ ስጋና ከመከራ ሞት ለማዳን እርዛት፣ ግርፋት፣ በደል፣ መገፋት አልፎም ስቅላትን ተቀብሏል። በመጨረሻም የብርሃን አምላክ የሆነው እየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ተነስቷል ።

እኛም ዛሬ በትምህርት ስርዓታችን ላይ ያጋጠመንን ችግር በመተባበርና በአንድነት ድል አድርገን ለልጆቻችን የተሻለ ሕይወት የእውቀት ብርሀን ልንለኩስ ይገባል።

የሀይማኖት አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ታዋቂ ግለሰቦች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ወላጆች ይህን የትምህርት መቋረጥ፣ በትምህርት ማህበረሰቡና በትምህርት ቤቶቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን የትምህርት ስብራት ችግር በቃ ልንል ይገባል።

ዛሬ በአግባቡ ያላስተማርነው የነገ ሀኪም ህመማችንን አይፈውስም፤ ዛሬ በአግባቡ ያላስተማርነው መሀንዲስ ነገ ከተሞቻችንን አይገነባም። በየሙያ ዘርፉ እኛን ከተቀረው ዓለም ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርጉን ልጆች የምናፈራው በትምህርት ነው።

ማንኛውም ለልጆቹ የነገ ተስፋና ዘላለማዊ ቅርስ ማውረስ የሚሻ የክልላችን ነዋሪ ሁሉ ለትምህርት ቅድሚያ በመስጠት ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ህጻናትን ወደ ትምህርት ቤት በመመለስ፣ ለመምህራን ጥላና ከለላ በመሆን የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ በመገንባት እንዲረባረብ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

ትምህርት በጊዜ የተገደበ ስራ ነው። በመሆኑም የ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ቀሪ ጊዜያችሁን በአግባቡ በመጠቀም ለፈተና እንድትዘጋጁ። መምህራን እና ወላጆችም ለእነዚህ ተማሪዎች አስፈላጊውን እገዛ እንድታደርጉላቸው እጠይቃለሁ።

መልካም የትንሳኤ በአል !!
ዶክተር ሙሉነሽ ደሴ
በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ

ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን አማራጮች ይጠቀሙ
1. በዌብ ሳይት ገጻችን http://www.anrseb.gov.et/
2. በዩቱብ ቻናላችን https://www.youtube.com/channel/UCARNQWN5bm5z2JmKsC_Cn8w
3. በፌስ ቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau
4. በቴሌግራም ቻናላችን t.me/anrse
ያግኙን
5. በቲክቶክ ገፃችን @amharaeducation bureau

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *