የሀገር እና የክልል አቀፍ ፈተና ለሚወሰዱ ተማሪዎች ድጋፍ እየተደረገ መኾኑን በምሥራቅ ጎጃም ዞን የደጀን ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ገልጿል።
በወረዳው ከ12 በላይ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ለክልል አቀፍ ፈተና እያዘጋጁ ነው።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን በደጀን ወረዳ ከ50 በላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ። በጸጥታ ችግር ምክንያት 20 ትምህርት ቤቶች ብቻ የመማር ማስተማር ሥራቸውን በተሟላ መንገድ እየፈጸሙ ነው።
የደጀን ወረዳ አሥተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ደመቀ መሠረት ሰላም በተረጋገጠባቸው ቀበሌዎች የመማር ማስተማር ሥራው እንዳይቋረጥ እና ተማሪዎች ለሀገር እና ለክልል አቀፍ ፈተናዎች እንዲዘጋጁ እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በጸጥታው ችግር ምክንያት ባለፈው ዓመት ወደ ሥራ ያልገቡ የትምህርት ተቋማትን ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል።
በዚህ ዓመት የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ፈተና ለሚወስዱ ተማሪዎች የክለሳ ትምህርት እሑድ እና ቅዳሜን ጨምሮ በመምህራን እንዲታገዙ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ወላጆችም ተማሪዎች ውጤታማ እንዲኾኑ እና በራስ መተማመን እንዲኖራቸው እገዛ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ ባጋጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት በወረዳው በርካታ የትምህርት ተቋማት ጉዳት እንዳጋጠማቸውም ጠቅሰዋል።
ትምህርት ቤቶች ተጠግነው ወደ ሥራ እንዲገቡ ኹሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
ሚያዝያ 15/2017
አሚኮ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *