በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለያየ ቦታ የሚገኙ ወጣቶችን የርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሠራም ቢሮው አስታውቋል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ትኩረት እያገኘ የመጣው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በስፋት እየተሠራበት ነው፡፡
በ2013 ዓ.ም የክረምት ወራትም ወጣቶችን በዘርፈ ብዙ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፎች ለማሰማራት ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ቢሮው አስታውቋል፡፡ ከሐምሌ 1 እስከ መስከረም 30 በሚዘልቀው የክረምት ወቅት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ በተለይም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ ወጣቶች የእረፍት ጊዜያቸውን ለማኅበረሰቡ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማኅበረሰባዊ እና ባህላዊ ልማቶች ፋይዳ ያላቸውን ተግባራት ያከናውናሉ፡፡
በዘንድሮው የክረምት ወቅት 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሳተፋሉ ያሉን በአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የወጣቶች ማካተት ንቅናቄ ዳይሬክተር አወቀ መንግሥቴ ናቸው፡፡ ይህም በአጠቃላይ በክልሉ ከሚገኙ እና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሰማራት ከሚችሉ ወጣቶች 67 በመቶውን ድርሻ የሚሸፍን ነው ብለዋል፡፡
የክረምቱ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሦስት ምዕራፎች እንዳሉት ያወሱት ዳይሬክተሩ ቅድመ ዝግጅት፣ ትግበራ እና በማጠቃለያ ምዕራፎች ይከፈላል ብለዋል፡፡ በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ተቋማትን ያሳተፈ እቅድ፣ የወጣቶች ምዝገባ፣ ግብዓት ማሟላት፣ ከክልል እስከ ቀበሌ መዋቅራዊ ቅንጅት እና ግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች እንደሚካሄዱ ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችም እስከ ግንቦት አጋማሽ ድረስ ይጠናቀቃሉ ተብሏል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ የክረምት የግብርና ሥራዎች፣ የትምህርት ተቋማት ጥገናና ማስዋብ፣ ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ተፈናቃዮች መጠለያ ጥገና፣ የድህረ ምርጫ ግንዛቤ ፈጠራ፣ የአካባቢ ሰላም እና መረጋጋት፣ ደም ልገሳ፣ የጎርፍ እና ቦይ ማፋሰስ፣ ጽዳት እና ውበት፣ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን መደገፍ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት እና ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት መሰል ተግባሮች በክረምቱ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሸፈኑ ተግባራት ናቸው ተብሏል፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኹለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት፣ እምቦጭ አረምን ማስወገድ፣ የኮሮናቫይረስ ስርጭት እና በውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት ዙሪያ ወጣቶች የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችንም እንደሚሠሩ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡ እንደ አቶ አወቀ ገለፃ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች ከሚያገኙት ክህሎት፣ የሀገር ፍቅር ስሜት እና ወገናዊ ድጋፍ ባሻገር በመንግሥት እና በሕዝቡ ሊወጣ የሚችለውን 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ያድናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አሚኮ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *