የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የግዝ ቋንቋን በትምህርት ቤቶች ለማስተማር ከምሁራንንና ባለድርሻ አካላት ጋር ያደረገውን ውይይት አስመልክቶ ለህዝብ ያደረሰው ዘገባ ነው፡፡
ግእዝ ጥበብ የተነገረበት፣ ሚስጥር የተቀመጠበት፣ ራእይ የተፃፈበት ቋንቋ ነው። ኢትዮጵያን ለማወቅ፣ ጥበብን ለመርመር፣ ምስጢር ለማመስጠር ግእዝን ማወቅ ግድ ይላል። የኢትዮጵያ ስልጣኔ፣ ጥበብ፣ ታሪክ፣ ፍልስፍና፣ ምርምር የተከተበው በግእዝ ነውና። የዓለም ሕዝቦች ኹሉ የመጀመሪያውን ቋንቋ ይፈልጉ ዘንድ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ። በቀደመችው ሀገር የቀደመ ቋንቋ እልፍ ቀዳሚ ምስጢራትን ይዞ ይገኛልና። ኢትዮጵያ ቀዳሚውን ቋንቋ የያዘች፣ ቀዳማዊት ሀገር ናት። በኢትዮጵያ የሥነጽሑፍ ታሪክ እንደ ግእዝ የዳበረ የለም። ለአያሌ ዘመናት ሚስጥራት የተፃፉት በግእዝ ቋንቋ ነው።
ታዲያ ቀዳሚው ቋንቋ መዳረሻውን አብያተክርስቲያናት ላይ አድርጎ ከብዙኃኑ ርቆ ቆይቷል። ኢትዮጵያውያንም የሀገራቸውን ሚስጥር መፍቻ ቁልፍ ረስተውት ቆይተዋል። ይልቁንስ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብቻ ሰጥተው ከግእዝ ርቀው ቆይተዋል። ቤተክርስቲያንም ከክብሩና ከምስጢሩ ሳታጓድል ይዛው ዘለቀች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም ጥበብን እንኩ፣ ኢትዮጵያን በምስጢር ለኩ እያለች ነው። ግእዝ የዓለማት፣ የፍጥረታት ኹሉ መገኛ የጥበብ መንገድ ነውና።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የግእዝ ቋንቋን እንደ አንድ የትምህርት አይነት ለማስተማር ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው። ትምህርት ቢሮው
<<ግእዝ ውእቱ ነቀዐ ጥበብ፣ ወአእምሮ፣ ወፍልስፍና ወኩሉ ምስጢር ዘያስተርኢ፣ ወዘኢያስተርኢ (ግእዝ የጥበብ፣ የዕውቀት፣ የፍልስፍና፣ የተጠና እና ያልተጠና ምስጢር ኹሉ ምንጭ ነው)፣ ርሒቅ እመልሳን ግእዝ ውእቱ ርሒቅ እምኩሎን ጥበባት ወምስጢራት ሀገር ዘታፈጥራ ውስቴታ ( ከግእዝ መራቅ ሀገር ውስጥ ከተፈጠሩ ሀገር በቀል ጥበባት መራቅ ነው)፣ ለከብናሁ ለግእዝ በሕይወቱ ለእመ ያረድኡነ ብዙኃን ዜና ሞቱ ( ብዙዎች የሞቱን ዜና ቢያረዱንም ግእዝን በሕይወቱ አገኘነው) ፣ ሐተታ ግእዝ ያበጽሕ ኃበ ዐበይት ማዕረጋተ አእምሮ ወልዕልና ሀገርነ ኢትዮጵያ (የግእዝ ጥናትና ምርምር ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ታላላቅ የከፍታና የዕውቀት ደረጃቸውን ያደርሳል) እያለ ነው።
ኢትዮጵያውያን ኹሉ ግእዝን ካወቁት በየገዳማቱና በየአድባራቱ እልፍ ጥበባትን ይዘው የተቀመጡ ምስጢራትን ይመረምራሉ። በጥበብ ዓይን ዓለምን ይመለከታሉ፣ መንገዳቸውን ያስተካክላሉ፣ በቀናው መንገድም ይጓዛሉ፣ የቀደመውን ቋንቋ የያዙት ሕዝቦች በጥበብ መንገድ ሲቀድሙም ሌሎች ይከተላሉ።
የግእዝ ቋንቋ የመገለጥ ዘመን የደረሰ ይመስላል። ጥበባት ሊዳሰሱ፣ ምስጢራት ሊነሱ ነው። ለዓመታት ጥበባትን በገዳማትና በአድባራት ይዘው የቆዩ ሊቃውንት እስከነ ጥበባቸው ወደማሳ ሊወጡ ነው፣ በማሳውም መልካም ዘር ሊዘሩ ነው። ያን ጊዜ ዘሩ ያማረ ፍሬውም የሰመረ ይሆናል።
ግእዝን የአንድ ሃይማኖት ቋንቋ ብቻ አድርገው የሚቆጥሩም አሉ። ግእዝ ግን ጥበብን የሚሹ ኹሉ እንጂ ለአንድ ሃይማኖት የተሰጠ አይደለም። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠበቀችው እንጂ የእኔ ብቻ ነው ብላ አልከለከለችም።
በምክክር መድረኩ መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ዶክተር ይልቃል ከፋለ ግእዝ በኢትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ድርሻ ያለው ነው ብለዋል።
የጽሑፍ ፈጠራ፣ የእደ ጥበብ ሥራዎች፣ የመንግሥት ምስረታ፣ የገንዘብና የንግድ ሥራ ጥንታዊ ስልጣኔ ተብለው ይጠቀሳሉ ያሉት ኀላፊው ጥንታዊ ስልጣኔ አሻራ ዋናው የጽሑፍ ሥራ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ሥልጣኔ የፈለቀባት ሀገር ስለመሆኗም አንስተዋል። በተለይም በቀደመው ዘመን በሳባ፣ በግሪክና በግእዝ ቋንቋ ይከተብ እንደነበር ነው የተናገሩት። ግእዝ በሥነጽሑፍ እያደገ መጥቶ ለአማርኛ መሠረት ሆኗልም ነው ያሉት።
የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ቀለም በጥብጠው፣ ብራና ፍቀው አያሌ መጻሕፍትን ጽፈዋል፣ መጻሕፍቱ በእድሜ ጠገብነታቸው ብቻ ሳይሆን በውስጣቸው በያዙት መንፈሳዊ፣ ጥበባዊና ሀገር በቀል ዕውቀት በመያዛቸው የኢትዮጵያ ውድ ሀብት ናቸው ብለዋል። በአያያዝ ጉድለት፣ በቃጠሎና በስርቆት ችግር የገጠማቸው መጻሕፍት ስለመኖራቸውም ገልጸዋል።
የግእዝ ዕውቀት ለዘመናዊ ዕውቀት መነሻ ሳይሆን ሲቀር ሊያስቆጭ ይገባልም ብለዋል። የግእዝን ውድና የከበሩ መጻሕፍትን ለመረዳት ግእዝን ማወቅ ይገባልም ነው ያሉት።
የሀገርን ፍቅርን ለመገንባት፣ ጥበብን ለማሳደግ የሀገር ውድ ሀብት ስለመሆኑም ገልጸዋል። ግእዝ ሊቃውንት ለፍተው ያሳደጉት ስለመሆኑም ተናግረዋል።
አውሮፓውያን ከጨለማውን ዘመን ሲወጡ የተሐድሶ ዘመን ያሉት የግሪክንና የሮማን ስልጣኔ ተመልሶ በማጥናት ነው ያሉት ዶክተር ይልቃል ከችግር ለመውጣት ሀገር በቀል እውቀትን መጠቀም አስፈላጊ ነው ብለዋል። ለእድገት የራስን ዕውቀት ማሳደግ ይገባልም ነው ያሉት። ቋንቋ በዘርና በአካባቢ የሚገደብ አለመሆኑንም አንስተዋል።
ትምህርት ቢሮው የግእዝ ቋንቋን በመደበኛ ትምህርት ከማስተማር በተጨማሪ የአረብኛ ቋንቋን እንደ አንድ የትምህርት አይነት ኾኖ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚሰጥ ይሆናል፣ በጥናት በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚሰጥበትን መንገድ እናመቻቻለንም ብለዋል። ይህም ልሳነ ብዙ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር ያስችላል ነው ያሉት።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ Amhara National Regional State Education Bureau
በዌብሳይት https://www.anrseb.gov.et/
በቴሌግራም https://t.me/anrse
ፌስቡክ https: Amhara-Education-Bureau