የ2013 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በሰላም ለማጠናቀቅ ባለ ድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ፡፡
_______________________________________________________________
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 2/2014 ዓ.ም ድረስ የሚሰጠውን የ2013 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና አሰጣጥን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አካሂዷል፡፡
በውይይቱ የተገኙት በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማእረግ የማህበራዊ ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን ወቅቱን ግምት ውስጥ ያስገባ አመራር በመስጠት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ፈተናው ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ እንዲሰጥ ሃላፊነታቸውን መወጣት እንደላባቸው አሳስበዋል፡፡
በፈተና ወቅት ተማሪዎች በማህበራዊ ሚዲያ በሚሰራጩ የተለያዩ ሃሰተኛ መረጃወች ሳይረበሹ በተረጋጋ ስነ ልቦና ፈተናውን እንዲወስዱ መምህራን፣ ወላጆችና የትምህርት ተቋማት የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች መስራት እንዳለባቸው አቶ ስዩም መኮንን አስገንዝበዋል፡፡
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ ፈተናው የነገ ሃገር መሪዎችን፣ ወታደሮችንና የልዩ ልዩ የሙያ ባለቤቶችን የምናፈራበት ስለሆነ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ምንም እንኳን የጸጥታ አካላት የህልውና ዘመቻ ላይ ቢሆንም የፈተናውን ደህንነት በመጠበቅና የፈተና ደንብ ጥሰቶች እንዳይኖሩ ለመከላከል በመናበብና በመቀናጀት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
ክልላችን ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት ከዚህ በፊት በፈተና አሰጣጥ ወቅት ይገጥሙ ከነበሩ ችግሮች በመማር ፈተናው በሰላማዊ ሁኔታ እንዲሰጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በከፍተኛ ትጋትና ሃላፊነት እንዲሰሩ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ማተብ ታፈረ /ዶክተር/ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአማራ ክልል የ2013 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናን ለመውሰድ 164 ሺህ 107 ተማሪዎች የተመዘገቡ ቢሆንም አሸባሪው ህወሃት በክልላችን በፈጸመው ወረራ ምክንያት 32 ሽህ 940 ተማሪዎች ፈተናውን በሌላ ጊዜ የሚወስዱ ይሆናል፡፡
የአሸባሪው ህወሃት የጥፋት ቡድን በወረራ በያዛቸው በሰሜን ወሎ ፣ በዋግህምራ፣ ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ወሎ ዞኖች በሚገኙ 112 ትምህርት ቤቶች ፈተናው በሌላ ጊዜ የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያና ዌብ ሳይት አማራጮች ለማግኘት ቀጣዮቹን ሊንኮች ይጠቀሙ ::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *