የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ዝርፊያና ውድመት ለደረሰባቸው የትምህርት ተቋማትና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ አደረገ፡፡
አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች ላይ ባደረሰው ወረራ የትምህርት ተቋማት ከፍተኛ የሆነ ዝርፊያና ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡ እነዚህን የትምህርት ተቋማት መልሶ ለመገንባት የበርካታ አካላትን ድጋፍ ይሻሉ፡፡
የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዬን ብር በላይ የገንዘብና አይነት ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን አሳይቷል፡፡ ድጋፉን ያስረከቡት የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሴ ጋጄት አሸባሪው ቡድን በተለይ በትምህርት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ መፈጸሙን አውስተው በመጀመሪያ ዙር ድጋፍ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ለአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ማስረከባቸውን ገልጸዋል።
 
የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ ያደረገው ድጋፍ የመጀመሪያ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙሴ በቀጣይም ለአማራና ለአፋር ክልል ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ ተጥናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በአማራ ክልል የወደሙ የትምህርት ተቋማትን ለመደገፍ የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ ከጎኑ እንደሚቆም አቶ ሙሴ አረጋግጠዋል።
አቶ ሙሴ በአማራና በአፋር ክልሎች የደረሰው ውድመትና ዝሪፊያ የክልሎቹ ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያውያን መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም የተጀመረው የአንድነት ጉዞ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አቶ ሙሴ ጋጄት ተናግረዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አቶ ሙላው አበበ የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ ላደረገው ድጋፍ በአማራ ክልል ተማሪዎች፣ መምህራንና በትምህርት ተቋማት ሠራተኞች ስም ምስጋና አቅርበዋል። ወራሪው ቡድን በወረረበት አካባቢ ሁሉ የትምህርት ተቋማትን ወንበሮች፣ ፕላዝማዎች፣ ኮምፒውተሮች፣ መረጃዎችንና ሌሎች ግብዓቶችን ሙሉ በሙሉ መዝረፍና ማውደሙን እንዲሁም የመቃብር ቦታ ማድረጉን ተናግረዋል።
የወደሙ የትምህርት ተቋማትን ወደ ነበሩበት ለመመለስ በክልሉ መንግሥት አቅም ብቻ ስለማይቻል የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ ሙላው ጥሪ አቅርበዋል። ድጋፉንም ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እንደሚደርስ አስረድተዋል። ይህም የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑን አቶ ሙላው አበበ ገልጸዋል።
በአሸባሪው የህወሓት ቡድንና ወራሪው የትግራይ ሃይል የተዘረፉና የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እኔም የድርሻዬን እወጣለሁ!!!
ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያና የዌብ ሳይት አማራጮች ለማግኘት ቀጣዮቹን ሊንኮች ይጠቀሙ ::
ፌስቡክ Amhara-Education-Bureau
ዩቱዩብ UCARNQWN5bm5z2JmKsC_Cn8w
በዌብሳይት https://www.anrseb.gov.et/
በቴሌግራም https://t.me/anrse

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *