ማላላ ፈንድ በአማራ ክልል የ19 ሚሊዮን ብር በላይ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡
___________________________
ማላላ ፈንድ በአማራ ክልል በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች እና የትምሕርት ተቋማትን ሊደግፍ የሚችል የ19 ሚሊዮን ብር በላይ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡
በአማራ ክልል የትምሕርት ዘርፍ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ፕሮጀክት የማስጀመሪያ መርኃግብር በባሕር ዳር ተካሄዷል። ፕሮጀክቱ በማላላ ፈንድ የሚደገፍ ሲኾን በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ ጉዳት ለደረሰባቸው ተማሪዎች፣ ትምሕርት ቤቶች እና ወላጆች የሚውል ነው ተብሏል።
በመርኃ ግብሩ ላይ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ ስዩም መኮንን በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በርካታ ሴቶች መገደላቸውን፣ መፈናቀላቸውንና መደፈራቸውን ተናግረዋል። ቡድኑ በተለይ በጤና እና በትምሕርት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱንም ጠቁመዋል። በርካታ ትምሕርት ቤቶች ጉዳት ስለደረሰባቸው ተማሪዎችን ተቀብለው ለማስተማር አለመቻላቸውን ጠቅሰዋል።
በሽብር ቡድኑ ወረራ ምክንያት በክልሉ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምሕርት ገበታቸው ውጭ መኾናቸውን አቶ ስዩም ገልጸዋል። በትምሕርት ቤቶች ላይ በደረሰው ውድመትና ዘረፋ ምክንያት አሁንም በርካታ ተማሪዎች በትምሕርት ገበታቸው ላይ መገኘት አለመቻላቸውን ነው የተናገሩት።
አቶ ስዩም እንዳሉት በማላላ ፈንድ የሚጀምረው ፕሮግራም ሴቶችን ከመደገፍ አንፃር ጠቀሜታው የጎላ ነው። ለፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል። ሌሎች ድርጅቶች፣ በጎ አድራጊ ማኅበራትም ኾኑ ግለሰቦች መሰል ድጋፍ በማድረግ ኀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ሴቶች ማኅበር ሊቀመንበር ትብለጥ መንገሻ በማላላ ፈንድ በሚቀጥሉት አራት ወራት በሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ሰሜን ጎንደር እና ደቡብ ጎንደር ለሚገኙ በሽብር ቡድኑ ጉዳት ለደረሰባቸው ለተማሪዎችና ለወላጆቻቸው የሚውል 19 ሚሊዮን 593 ሺህ ብር በላይ በቀጥታ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት መደረጉንም ገልጸዋል።
ሌሎች በሽብር ቡድኑ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎችን ለመደገፍ የሚያስችል ተጨማሪ ፕሮጀክቶች በመቅረጽና ሃብት በማፈላለግ ተደራሽ እንዲኾኑ ጥረት እንደሚደረግ ሊቀመንበሯ አመላክተዋል።
የአደጋ ምላሽ ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ ሲገባ 3 ሺህ ተማሪዎች፣ 2 ሺህ ልጃገረዶች፣ 500 ሕጻናትና 1 ሺህ 500 ቤተሰቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት። ፕሮጀክቱ ለ10 ትምሕርት ቤቶች የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግና ተፈጻሚነቱ የተሳካ ከኾነ ቀጣይነት ያለው መኾኑን ወይዘሮ ትብለጥ ገልጸዋል።
ማላላ ፈንድ በአማራ ክልል በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች እና የትምሕርት ተቋማትን ሊደግፍ የሚችል የ19 ሚሊዮን ብር በላይ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡
ዘገባው የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ነው
የወደሙ ትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በአጭር የጽሑፍ መልዕክት አቅምዎ የፈቀደውን የብር መጠን ጽፈው ወደ 9222 ይላኩ።
በቴሌብር ድጋፍ ለማድረግ የቴሌብር ቁጥራችን 9222 ን ይጠቀሙ በተጨማሪም በቴሌብር ዓለምአቀፍ ሀዋላ ከውጭ ሀገራት ድጋፍ ለማድረግ 0993161616 በመጠቀም የድርሻዎን ይወጡ።
ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያና ዌብ ሳይት አማራጮች ለማግኘት ቀጣዮቹን ሊንኮች ይጠቀሙ ::
በዌብሳይት https://www.anrseb.gov.et/
በቴሌግራም https://t.me/anrse

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *