በአማራ ክልል 3 የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው
ባህር ዳር፤ መስከረም 28/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በሆነ በጀት የሦስት አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የአዳሪ ትምህርት ቤቶቹ መገንባት ተወዳዳሪና ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር ተገልጿል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመ፤ የአዳሪ ትምህርት ቤቶቹ ግንባታ እየተከናወነ ያለው በሰቆጣ፣ ደብረታቦርና ፍኖተ ሰላም ከተሞች እንደሆነ ለኢዜአ ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶቹ ደረጃቸውን የጠበቁ የመማሪያ ክፍሎች፣ የአስተዳደር፣ የቤተ መፃህፍት፣ የቤተ ሙከራ፣ የአይሲቲ፣ የማደሪያ፣ የመዝናኛ፣ የስፖርት ማዘውተሪያና ሌሎችንም መገልገያዎች በማካተት እየተገነቡ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ግንባታቸው ከ2016 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ እየተካሄደ ያሚገኘው የአዳሪ ትምህርት ቤቶቹ አፈፃፀም በአሁኑ ወቅት እስከ 20 በመቶ መድረሱን አመልክተዋል።
የትምህርት ቤቶቹን ግንባታ በማጠናቀቅ በ2019 የትምህርት ዘመን ወደ መማር ማስተማር ስራ ለማስገባት መታቀዱን የጠቆሙት አቶ መኳንንት፤ ትምህርት ቤቶቹ እያንዳንዳቸው 400 ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም እንዲኖራቸው ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የአዳሪ ትምህርት ቤቶቹ መገንባት ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ለአገር የሚጠቅሙ ተወዳዳሪና ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።
በክልሉ ቀደም ሲል ተገንብተው ስራ የጀመሩ የደሴ፣ የደብረ ብርሃንና የደብረማርቆስ የአዲስ ዓለማየሁ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ብቃት ያላቸውን ተማሪዎች እያፈሩ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
የዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰይፉ ሞገስ እንዳሉት፤ በሰቆጣ እየተገነባ ያለው አዳሪ ትምህርት ቤት በጥሩ አፈጻጸም ላይ ይገኛል።
የግንባታ አፈፃፀሙ አሁን ላይ 20 በመቶ መድረሱን ጠቅሰው፤ ትምህርት ቤቱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ የቅርብ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተገልጸዋል።
የአዳሪ ትምህርት ቤቱ በአካባቢው መገንባት በቀጣይ የሚቀበላቸውን ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን በጥራት ለማስተማርና ለማብቃት ይሰራል ብለዋል።
ከትምህርት ቢሮው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአማራ ክልል በትምህርት ዘመኑ 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለማስተማር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው።
ኢዜአ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *