የካቲት 11/2017 ዓ.ም (ትምህርት ቢሮ) የአደገኛ ዕፆች፣ መድኃኒቶች እና የትምህርት አዋኪ ምክንያቶች በመከላከል በስነ ምግባሩ የተመሰገነ ትውልድ ማፍራትን ዓላማ ያደረገ ውይይት በባህር ዳር እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ትምሕርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ እየሩስ መንግስቱ
የአደገኛ ዕፆች፣ መድኃኒቶች እና የትምህርት አዋኪ ነገሮች መስፋፋት መማር ማስተማሩን ከመጉዳት ባለፈ የወጣቶችን ጤናን እያቃወሰ መሆኑን ገልጸዋል።
ዜጎች በመልካም ስነ ምግባር ከሚታነጹባቸው ቦታዎች አንዱ የትምህርት ተቋማት ናቸው። የአደገኛ ዕፆች፣ መድኃኒቶች እና የትምህርት አዋኪ ምክንያቶች በመከላከል በስነ ምግባሩ የተመሰገነ ትውልድ ለማፍራት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ጥረት እንዲያደርግ ወይዘሮ እየሩስ ጥሪ አቅርበዋል።

አደገኛ ዕፅ የሰውን የነርቭ ስርዓት በመጉዳት አካላዊ፣ አዕምሮአዊ እና የተለያዩ ውስጣዊ እና ውጫዊ የጤና ችግር የሚያስከትል መሆኑን የተለያዩ ጥናቶች ያስረዳሉ።

አደንዛዥና አደገኛ የሆኑ ሱስ አስያዥ ዕፆችን የሚጠቀሙ ተማሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመር በአገራችን ብሎም በክልላችን አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የቋንቋና ማህበራዊ ሳይንስ ቡድን መሪ አቶ ውባለ ሙሔ ገልጸዋል ፡፡ ሱስ አስያዥ እፅ የሚጠቀሙ ተማሪዎች ከዚያ በፊት በተፈጥሮ እና በሂደት ካዳበሩት አንፃራዊ የሆነ ጤነኛ ባህሪ ለየት ባለ ሁኔታ ዕፁ በሚያሳደርባቸው ተፅዕኖ ምክንያት ከማህበረሰቡ ባህልና እሴት ውጭ የሆኑ ወይም ነውር የሆኑ ባህርያትን እንዲፈፁሙ እና የወሰዱት ባዕድ ነገር ያልተገባ ሁኔታ እና ቦታ ላይ ሲያውላቸው ይታያሉ።

ተማሪዎች ሁሉን ነገር ለማወቅ ካላቸው ጉጉት የተነሳ ሀገር በቀል ለሆኑም ሆነ ከሀገር ውጪ ለሚመጡ አደንዛዥ ዕፆች፣ ለትምባሆ፣ ለአልኮል መጠጥና ለልዩ ልዩ ሱሶች የሚጋለጡበት ሁኔታ ይበዛል፡፡ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም በተማሪዎች ትምህርት አቀባበል ላይ ከፍተኛ ተፅእኖም ያሣድራል፡፡

አደንዛዥ እፅ ከሚጠቀሙት ተማሪዎች ይልቅ የማይጠቀሙት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉ ጥናቶች ያሣያሉ፡፡ ለሱስ ተጋላጭ መሆናቸው ደግሞ የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥ እንዲጨምርና ለትምህርት ጥራት መጓደል ምክንያት ነው። ከዚህም በላይ ተማሪዎች በለጋ ዕድሜያቸው ለአደገኛ ዕፆች ተገዥ ከሆኑ አዕምሮዓቸውን በትምህርት መገንባት በሚችሉበት ወቅት የአደገኛ ዕፆች ተጠቃሚና ተጠቂ የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ስለሚሆን ከመምህራኖቻቸው ጋር ተግባብቶ የመማር እና የሥነ ምግባር ችግር በስፋት ይስተዋልባቸዋል፡፡

ተማሪዎችን ከአደገኛ ዕፆችና መድኃኒቶች ለመጠበቅ በስነ ምግባሩ የተመሰገነ ትውልድ ለማፍራት በትምህርት ቤት የሚንቀሳቀሱ ክበባት፣ መገናኛ ብዙሀንና የሀይማኖት ተቋማት የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው የግብረ ገብ መምህር የሆኑት ሻሺቱ አለም አስገንዝበዋል።

ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሚከተሉትን አማራጮች ይጠቀሙ
1. በዌብ ሳይት ገጻችን http://www.anrseb.gov.et/
2. በዩቱብ ቻናላችን https://www.youtube.com/channel/UCARNQWN5bm5z2JmKsC_Cn8w
3. በፌስ ቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/Amhara-Education-Bureau
4. በቴሌግራም ቻናላችን t.me/anrse
ያግኙን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *