በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የትምህርት ዘርፉ ተጎድቷል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ተዝግተዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ጌታሁን ፈንቴ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በዞኑ የትምህርት ሥራ ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል ብለዋል። ከ996 ትምህርት ቤቶች መካከል እያስተማሩ ያሉት ከ156 የማይበልጡ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ከ630 ሺህ በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አለመሄዳቸውንም ተናግረዋል። ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ ከማኅበረሰቡ ጋር ውይይት እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። የተሻለ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ተማሪዎች እንዲመዘገቡ እና ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ተማሪዎች የትምህርት አቀባበላቸው ተጽዕኖ ውስጥ እንዳይገባ የማብቃት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። የተመዘገቡ ተማሪዎችንም ኾነ ሌሎች ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለማምጣት አሁንም ፈተና እንዳለ አንስተዋል።
ማኅበረሰቡ በትምህርት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት እንዲረዳ ሰፋፊ ውይይቶች መደረጋቸውንም ገልጸዋል። ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ የማግባባት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ትምህርት የገጠመውን ችግር በልኩ በመገንዘብ ለመፍትሔው መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት። ችግሩን በልኩ የተገነዘበ መሪ ሲኖር ከችግሩ የሚያወጣ መፍትሔ ያመነጫል ብለዋል።
በዞኑ ከ621 በላይ ትምህርት ቤቶች ከዘረፋ እስከ ውድመት ድረስ ጉዳት እንደደረሰባቸውም አስታውቀዋል። እየገጠመ ያለው ችግር የትምህርት ቤቶች መዘጋት ብቻ ሳይኾን በትምህርት ቤቶች ላይም ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው ብለዋል።
ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶችን መልሶ የመገንባት ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የትምህርት መምሪያ ኀላፊ ደስታ አሥራቴ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በትምህርት ላይ ስብራት ፈጥሯል ነው ያሉት። ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለማምጣት እና ስብራቱን ለመጠገን ጥረቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ 732 ሺህ ተማሪዎችን ለመመዝገብ አቅደው 199 ሺህ 220 ተማሪዎችን መመዝገባቸውንም ተናግረዋል። የተመዘገቡት ተማሪዎች 27 ነጥብ 3 በመቶ ብቻ መኾናቸውን ገልጸዋል። እነዚህን ተማሪዎች ለማስመዝገብ መስዋዕትነት መከፈሉንም ተናግረዋል። መምህራን ይደበደባሉ፣ ይንገላታሉ፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ይደርስባቸዋል ነው ያሉት።
ሕጻናት እንዳይማሩ ማድረግ በየትኛውም መንገድ ተገቢ አይደለም ብለዋል። ሕጻናት እንዳይማሩ ማድረግ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መኾኑንም ገልጸዋል። ተማሪዎች እንዲማሩ ማንኛውም አካል መሥራት እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል።
የተከፈቱ ትምህርት ቤቶችም በጸጥታ ችግር ምክንያት አንድ ሳምንት ይከፈታሉ፣ መልሰው ይዘጋሉ ያሉት ኀላፊው ይህ ደግሞ በተማሪዎች ላይ ጫና እያሳደረ ነው ብለዋል። የትምህርት ሥራ በቀውስ ወቅት ብቻ ሳይኾን በሰላምም ጊዜ ቅንጅታዊ ሥራዎችን ይጠይቃል ነው ያሉት።
በዚህ የቀውስ ጊዜ አጋር አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል። ትምህርት ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር በተገቢው መረዳት ይጠይቃልም ብለዋል። አሁን ያለው የትምህርት ሁኔታ የነገን እጣ ፋንታ የሚወስን በመኾኑ ለትምህርት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት።
ማኅበረሰቡ ትምህርት ቤቶች እንዳይዘጉ የሚጠብቅ እና ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት የሚልክ ከኾነ ችግሮች ይፈታሉ ብለዋል። ማኅበረሰቡ ልጆቻችን መማር አለባቸው ብሎ አቋም በያዘባቸው አካባቢዎች ላይ ተማሪዎች እየተማሩ መኾናቸውንም አንስተዋል።
ማኅበረሰቡ የግብርና ግብዓት ሲያጣ ግብዓት አጣሁ ብሎ እንደሚሞግተው ሁሉ ትምህርት ቤቶች ሲዘጉም ለምን ብሎ መሞገት አለበት፣ ልጆቼ ለምን አይማሩም ብሎ ሊቆጨው ይገባል ነው ያሉት።
ሕጻናት ወደ ትምህርት ቤት ባለመምጣታቸው ምክንያት ያለ ዕድሜ ጋብቻ እንዲስፋፋ እያደረገ መኾኑንም አንስተዋል። ማኅበረሰቡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ እና ትምህርት ቤቶች እንዲጠበቁ የማድረግ ኀላፊነት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።