የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከኮሙኒኬሽን፣ ሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት መሪዎች እና ባለሙያዎች ጋር በትምህርት ለትውልድ ዘመቻ ላይ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የሀገራት ዕድገት ምንጩ ትምህርት ነው ብለዋል።
እንደ ሀገር ኢትዮጵያ፣ እንደ ክልል ደግሞ አማራ ፤ ሀገር በቀል እውቀት እና ጥንታዊ ትምህርትን ቀድመው ተደራሽ ካደረጉት መካከል ነበሩ ፤ የሥልጡን ሕዝብ መገኛ እና መፍለቂያም እንደ ነበሩ በርካታ ማሳያዎች አሉ ነው ያሉት።
አሁን ላይ የክልሉን የትምህርት ሥራ አደጋ ላይ የጣሉ ወቅታዊ እና ነባር ችግሮችን ተጋፍጠናል ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ፤ በተለይም ወቅታዊ የጸጥታ ችግሩ ነባሩን የትምህርት ሥርዓት ችግሮች በፍጥነት ለመፍታት የምናደርገውን ጥረት ውስብስብ አድርጎታል ነው ያሉት።
ዶክተር ሙሉነሽ በንግግራቸው የሀገራት ዘላቂ እድገት እና ሁሉን አቀፍ ውድድር እርካቡ ትምህርት ኾኖ ሳለ መማር ማስተማርን ማወክ ከሕዝብ መራቅን የሚያመላክት ነው ብለዋል። ትምህርት ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነጻ ኾኖ ሳለ የግል ፖለቲካዊ ፍላጎት ማሳኪያ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ከሕዝቡ ሥነ ልቦናዊ ስሪት የራቀ ድርጊት እንደኾነም አንስተዋል።
“ትምህርትን ማቃናት ሀገርን ማጽናት ነው” ያሉት ኀላፊዋ በችግር ውስጥም ኾነን ሙያዊ ግዴታቸውን ለመወጣት እና ትውልድ ለማስቀጠል እስከ ሕይዎት መስዋዕትነት የከፈሉ መምህራን አሉ ብለዋል። የተሳደዱ፣ የተንገላቱ፣ የታገቱ እና ውድ ዋጋ የከፈሉ የትምህርት ባለሙያዎች እና መምህራን መኖራቸውን ጠቅሰው ጥረታቸው በሕዝቡ እና በሌሎች አጋር አካላት መታገዝ ይኖርበታል ብለዋል።
የክልሉ ሕዝብ እና የኢትዮጵያ ሰላም ውሎ ማደር እረፍት የሚነሳቸው የውስጥ እና የውጭ ኀይሎች ዘላቂ መታገያ አድርገው የወሰዱት ትምህርትን ነው ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ትግል ይፈልጋል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የሚዲያ እና የሕዝብ ግንኙነት ሴክተሩ ሚናው የጎላ መኾኑን አንስተዋል።
ወላጆች በልጆቻቸው ትምህርት ላይ የሚቃጣ ጥቃት ሁሉ ምን ያክል እንደሚጎዳ ያውቃሉ። ነገር ግን ሕዝብን አነቃንቆ ትምህርትን ከተፅዕኖ ነጻ ለማድረግ የኮሙኒኬሽን ዘርፉ የጎላ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። እስካሁን የነበሩ ጥረቶች ተስፋ ሰጪ ቢኾኑም ካለው ውስብስብ ችግር አንጻር በጋራ መሥራት እና የበለጠ መበርታትን ይጠይቃል ነው ያሉት።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *