ፍቅር ደብረ ብርሃን በጎ አድራጎት ማህበር ከትምህርት መምሪያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የንባብ አውደ ርዕይ ተካሄደ፡፡
የፍቅር ደብረብርሃን በጎ አድራጎት ማህበር ፕሬዝዳንት እና የደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ መምህር ካሳሁን በቀለ (ዶ/ር) እንደገለጹት ማህበራቸው የሰውን አዕምሮ እናልማ በሚል ውጭ በሚኖሩ የደብረብርሃን ተወላጆች አነሳሽነት የተመሰረተ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በጎ አድራጎት ማህበሩን ለየት የሚያደርገው የህፃናትንና የወጣቶችን አዕምሮ በማልማት በቴክኖሎጂው ዘርፍ ተወዳዳሪ ዜጋ መፍጠር የሚል ዓላማ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በአራት ዓመት ጉዞው ህፃናትን በበተለያዩ የኮምፒዩተር ፕሮግራሞች 2 ጊዜ አሰልጥኖ ማስመረቁንና ወጣቶችም ላይ ጥሩ ጅምር ስራዎች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡
በአሜሪካና በአውሮፓ የሚኖሩ የደብረብርሃን ተወላጆች ባደረጉት ድጋፍ በርካታ ኮምፒዩተሮችና ለአንደኛ እና ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች አጋዥ መፃህፍት መጥተው በ04 ወጣት ማዕከል አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ለ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ በሺዎች የሚቆጠሩ አጋዥ መጻህፍት፣የላብላቶሪ ሲሙሌሽን፣ከ7 እስከ 10 ዓመት ለሀገር አቀፍ ፈተና ዝግጅት የሚጠቅሙ ፈተናዎች የተጫኑባቸው 25 ከምፑዩተሮች በዚሁ ወጣት ማዕከል የተዘጋጁ ቢሆንም ተማሪዎች እየተጠቀሙባቸው አይደለም ብለዋል፡፡
ፍቅር ደብረብርሃን በጎ አድራጎት ማህበር ከደብረብርሃን ከተማ ትምህርት መምሪያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የንባብ አውደ ርዕይ ዓላማ ተማሪዎች ምቹ ሁኔታውን ተጠቅመው አንብበው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡
የደብረብርሃን ከተማ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መቅደስ ብዙነህ በበኩላቸው እንደገለጹት የከተማው ተማሪዎች አንብበው የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ በውጭ የሚኖሩ የደብረብርሃን ተወላጆች ከ3 ሺህ የሚበልጡ አጋዥ መፃህፍት አሰባስበው በመላካቸው አመስግነዋል፡፡
ተማሪዎችና መምህራን በመፃህፍቱ እንዲጠቀሙ የንባብ አውደ ርዕዩ እንዲዘጋጅ ላደረጉ የማህበሩ የስራ ኃላፊዎች ጨምረው ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ የንባብ ባህላችን እየቀነሰ መምጣቱን ጠቅሰው ችግሩን ለመፍታት የንባብ አውደ ርዕይ መዘጋጀቱን አንስተዋል፡፡
አሁን ያለንብት ዘመን የቴክኖሎጂ፣ከፍተኛ ዕውቀት የሚጠይቅና ውድድር የበዛበት ስለሆነ እንደ በፊቱ በቀላሉ የሚኖርበት አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለመወዳደር ደግሞ የቴክኖሎጂ ክህሎትን ማዳበር፣ አንብቦ ራስን ማብቃት፣ጠንክሮ ሰርቶ በአግባቡ መዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ተፎካካሪ ትውልድ ለመፍጠር የንባብ ባህልን በማሳደግ የመጡ መፃህፍትንና በኮፑዩተሮቹ የተጫኑ ፕሮግራሞችን መጠቀም ይገባል በማለት ወይዘሮ መቅደስ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በአውደ ረዕዩ ላይ የተገኙ መምህራን እና ተማሪዎች መረጃውን ሌሎች በማድረስ ብዙዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የድርሻችሁን ሚና ልትወጡ ይገባል ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *