ትምህርት ቤቶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታዎችን ሊፈጥሩ እንደሚገባ ወላጆች ጠየቁ።
1 ሺህ 866 ተማሪዎችን ይዞ እያስተማረ የሚገኘው የነፋስ መውጫ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪወችን ውጤት ለማሻሻል ያለመ የወላጅ ተማሪ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ የ1ኛው ወሰነ ትምህርት የተማሪዎችን አፈፃፀም ለወላጆች አቅርቦ ገምግሟል።
የትምህርቱ ቤቱ ርዕሰ መምህር ሞገሴ ልየው የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ቤተ መጽሐፍት እሁድ እና ቅዳሜን ጨምሮ ክፍት ኾነው አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል። መምህራን ከመደበኛው የትምህርት ክፍለ ጊዜ በተጨማሪ የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጡ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ባለፋት ወራት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በጀት ትልቅ ፈተና ነበር ያሉት ርዕሰ መምህሩ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ወላጆች አጋዥ እንዲኾኑ ጠይቀዋል።
የትምህርት ቤቱ የወላጅ መምህራን ኅብረት ሰብሳቢ አቶ አከለ ፈንቴ ለተማሪዎች ሥነ ምግባር እና ውጤት መሻሻል ወላጆች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።
የውይይቱ ተሳታፊዎቹ የተማሪዎችን ሥነ ምግባር እና ውጤት ለማሻሻል የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን ገልፀው ትምህርት ቤቶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታዎችን ሊፈጥሩ እንደሚገባም ጠይቀዋል።
እንደ ላይ ጋይንት ወረዳ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት መረጃ በመጨረሻም በመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቷል።
በላይ ጋይንት ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት የሥርዓተ ትምህርት ቡድን መሪ ጌታሰው አዘዘው በወረዳው ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ አልመጡም ብለዋል። ተማሪዎች ለስደት፣ ያለድሜ ጋብቻ እና መሰል ማኅበራዊ ችግሮች ተጋላጭ ኾነዋል ያሉት ቡድን መሪው የመማር እድሉን ያገኛቹህ ተማሪዎች በቁጭት ውጤታቹህን ልታሻሽሉ ይገባል ብለዋል።
ለአካል ጉዳተኞች ትምህርት ቤቶች ምቹ እንዲኾኑ በትኩረት እየሠራ መኾኑን የገለጹት አቶ ጌታሰው ችግሩ የሁሉንም እርብርብ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።