በኮምቦልቻ ከተማ 132 ሚሊዮን ብር በሚኾን ወጭ ጤና ጣቢያ እና ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።
በኮምቦልቻ ከተማ የቦርከና ክፍለ ከተማ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች በመልሶ ለማቋቋም ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ትምህርት ቤቶችን እና ጤና ጣቢያ ለመገንባት ነው የመሰረተ ድንጋይ የተጣለው።
አሚኮ ያነጋራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች የማኅበረሰቡ የረዥም ጊዜ ጥያቄዎች ምላሽ በማግኘታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ልጆቻቸው ትምህርት ለማግኘት ወንዝ ተሻግረው በመጓዝ ለአደጋ ተጋላጭ እንደነበሩ አስታውሰው ልማቱን በገንዘብ እና በጉልበት በመደገፍ ከግብ እንዲደርስ እንሠራለን ብለዋል።
የቦርከና ክፍለ ከተማ ምክትል ሥራ አሥፈፃሚና የማኅበራዊ ዘርፍ ኀላፊ መሐመድ ጌታቸው በሰሜኑ ጦርነት ከወደሙ አካባቢዎች አንዱ የኮምቦልቻ ከተማ መኾኑን ገልጸዋል፤ ቦርከና ክፍለ ከተማም የጉዳቱ አንድ አካል ነው ብለዋል።
ይህንን ጉዳት ለመቅረፍ በስድስት ቀበሌዎች አንዳንድ ትምህርት ቤት እና በአንድ ቀበሌ ደግሞ አንድ ጤና ጣቢያ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ መጣሉን ገልጸዋል።
ከዓለም ባንክ በተገኘ የ132 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ተቋማቱ እንደሚገነቡም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በቦርከና ክፍለ ከተማ የጎፍ ቀበሌ በማኅበረሰብ ተሳትፎ መዋዕለ ሕፃናት፣ የቀበሌ አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት እና የፖሊስ ተቋም ግንባታ 22 ሚሊዮን ብር በሚኾን ወጭ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተጥሏልም ብለዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ.ር) ባስተላለፉት መልዕክት “የሚማሩ፣ የሚሠሩ እና የሌላን አጀንዳ የማይሸከሙ ልጆች እንዲኖሩን መሥራት አለብን፣ ለዚህ ደግሞ ትምህርት ቀዳሚው ነው” ብለዋል።
“ለትምህርት የሰጣችሁት ትኩረት የሚደነቅ ነው። ልጆቻችንን በትምህርት ስንገነባ ትውልድ እየተካን ነው” ሲሉም አክለዋል።
“የጀመራችሁትን እንደምትጨርሱ እምነት አለኝ መንግሥትም ከጎናችሁ ይቆማል፤ ትምህርትን አቅንተን ስንሄድ ሀገራችንን ከፍ ማድረግ እንችላለን። ” ሲሉ በመድረኩ ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *