የደብረ ብረሃን ከተማ ትምህርት መምሪያ በበኩሉ ለ2018 የትምህርት ሥራ ቅድመ ዝግጅት እያደገ መኾኑን ገለጸ።
የደብረ ብርሃን ዳሽን ቢራ ፋብሪካ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታነህ ዝቄ እንደገለጹት አክሲዮን ማኅበሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በዚህ ዓመት በከተማው ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ደረጃውን የጠበቀ ቤት ሰርቶ ከማስረከቡም በተጨማሪ ለቤት መሥሪያ እና ለሥራ ዕድል ፈጠራ የተለያዩ ግብዓቶች፣የልብስ ስፌት ማሽኖች ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ከፋብሪካው በሚወጣ የታከመ ውሃ ተጠቅመው በመስኖ በርካታ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መኾናቸውን፣በዝቅተኛ ዋጋ ተረፈ ምርቱን ለእንስሳት አርቢዎች በማከፋፈል ተጠቃሚነታቸው እንዲያድግ ማድረጋቸውን አብራርተዋል።
በዛሬው ዕለትም ከዚህ በፊት እንደሚደርጉት የመማር ማስተማሩን ሥራ ለመደገፍ 1 ሚሊዮን 120 ሺህ ብር ግምት ያለው 20 ሺህ ደብተር እና 6 ሺህ እስኪርቢቶ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
በቀጣይም በሰሜን ሸዋ ዞን ለተመረጡ ወረዳዎች፣ዋግ ኽምራ፣ሰሜን ወሎ፣ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደሮችን ያካተተ ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አቶ ጌታነህ አመልክተዋል።
በዚህ ክረምት ለመጪው 2018 ዓ.ም የትምህርት ሥራ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን የደብረ ብርሃን ከተማ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መቅደስ ብዙነህ አስረድተዋል።
ከዚህ ውስጥ አንዱ 23 ሺህ የትምህርት ግብዓት ለማሰባሰብ ታቅዶና ከአጋር አካላት ጋር ምክክር ተደርጎ እስካሁን ከ10 ሺህ በላይ ደብተር ማሰባሰብ መቻሉን አንስተዋል።
በምክክር መድረኩ መግባባት ላይ በተደረሰበት መሠረትም ዳሽን ቢራ ፋብሪካ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው 2 ሺህ ተማሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ደብተርና እስክርቢቶ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
ዳሽን ቢራ አክሲዮን ማኀበር ግንባር ቀደም ኾኖ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረጉ በተማሪዎቹ ስም ወይዘሮ መቅደስ ከፍ ያለ ምስጋ አቀርባለሁ ብለዋል።
በተመሳሳይ ሰን ዱቄት ፋብሪካ 12 ደርዘን ደብተርና 5 ፓኬት እስክርቢቶ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው ፋብሪካውን አመሥግነዋል።ሌሎች ድርጅቶችም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።