በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባለፉት ዓመታት በግጭት ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራቸውን በሚፈለገው ልክ መከወን አልቻሉም።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ጌታሁን ፈንቴ በግጭቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች በመጠገን እና በማደስ የውስጥ ግብዓትም በማሟላት በ2018 የትምህርት ዘመን ወደ መደበኛ ሥራ ለማስገባት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶች የውስጥ ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ እና ባላቸው የመሬት ሃብት ተጠቃሚ እንዲኾኑ የግብርና ሥራ እየሠሩ መኾኑንም ገልጸዋል።
በዚህም በስምንት ወረዳዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከ225 ሄክታር መሬት በላይ በዘር የመሸፈን ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ትምህርት ቤቶች እሰከ ነሐሴ ወር መጨረሻ ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው በመስከረም ወር መጀመሪያ መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዲጀምሩ እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎችን እና ወላጆችንም በማወያየት ያለፈውን ጊዜ ለማካካስ ይሠራል ብለዋል።
በክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራ የኮሌጅ እና የሁለተኛ ደረጃ በጎ ፈቃደኛ መምህራንን በማሳተፍ የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ ነው ያሉት ኀላፊው ከ7ሺህ በላይ ተማሪዎች በመማር ላይ ናቸው ነው ያሉት።
ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ ለማድረግም ችግኝ በመትከል ውብ እና ጽዱ ገጽታ የማላበስ እየተሠራ መኾኑንም አስገንዝበዋል።
ነሐሴ 7/2017ዓ.ም