በቴክኖሎጅ ዘርፍ ተሰማርቶ በትምህርት ላይ በርካታ ስራዎችን በመስራት የሚታወቀው ቀለም ሜዳ ቴክኖሎጅ ከ3 መቶ ሽህ ብር በላይ ዋጋ የሚያወጣ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስረክቧል፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት የቀለም ሜዳ ቴክኖሎጅ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ገብረመድኀን መኮንን ተማሪዎች በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆኑ ለማስቻል የተጀመረውን የአንድ ደርዘን ደብተር ለአንድ ተማሪ ንቅናቄ በመቀበል ከ3 መቶ ሽህ ብር በላይ ዋጋ የሚያወጣ 450 ደርዘን ደብተርና 450 እስክብሪቶ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመ ቀለም ሜዳ ቴክኖሎጅ የክልሉን የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ፈተና እርማት በቴክኖሎጅ የተደገፈ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ስራ መስራቱን ገልጸዋል፡፡ ጊዜና ወጭ ቆጣቢ የሆነው የማረሚያ ቴክኖሎጅ የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል የተማሪዎች ፈተናን በሁለት ሳምንት ውስጥ ብቻ አርሞ ውጤት ይፋ ማድረግ ማስቻሉን አመላክተዋል፡፡ ዛሬ ደግሞ ድርጅቱ ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረጉ አመስግነዋል፡፡