ትምህርት ቤቶች በሶስት ዙር ትምህርት እንዲጀምሩ ሊደረግ ነው፡፡
==================
ትምህርት ቤቶችን ዳግም መክፈት በሚቻልበት የውሳኔ ሃሳብ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት በጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ውይይት እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፋዎችና ሌሎች ሚኒስትሮችም ተገኝተዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ትምህርት ቤቶችን ዳግም ለመክፈት ስለቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ገለፃ አድርገዋል።

የትምህርት ቤቶች ትምህርት ማስጀመር ሂደት በሶስት ዙር እንደሚከናወን የሚል ምክረ ሃሳብ ቀርቧል፡፡

በገጠር ወረዳና ቀበሌ ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመጀመሪያው ዙር ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም ትምህርት እንዲጀምሩ የውሳኔ ምክረ ሃሳብ ቀርቧል።

በሁሉም የዞንና የክልል ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በ2ኛ ዙር ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ትምህርት እንዲጀምሩ ነው ምክረ ሃሳብ የቀረበው።

በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ ትምህርት ቤቶችም ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ትምህርት እንዲጀምሩ የውሳኔ ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።

የ8ኛና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን አስመልክቶም ሁሉም ተፈታኞች ለፈተና እንዲቀመጡ የሚል የውሳኔ ምክረ ሃሳብ መቅረቡ ተገልጿል።

የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሕዳር 22 እና 23 ቀን 2013 ዓ.ም የሚሰጥ ሲሆን ፈተና ላይ መቀመጥ የሚችሉት 7ኛ ክፍልን ተምረው ያጠናቀቁና የ8ኛ ክፍልን የአንደኛ ሴሚስተር ትምህርት የተከታተሉ ብቻ ናቸው።

የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መውሰድ የሚችሉት የ11ኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቁና የ12ኛ ክፍልን የመጀመሪያ ሴሚስተር ትምህርት የተከታተሉ ብቻ ናቸው ተብሏል።

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከሕዳር 28 እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚሰጥም በምክረ ሀሳቡ ላይ ተጠቅሷል።

የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱን በተመለከተ ለመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚወጣው መመዘኛ በግል ትምህርት ቤቶችም ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *