በሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮጀክት የሚገነቡ የትምህርት ተቋማት አፈፃፀም ውጤታማ መሆኑ ተገለጸ
የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም አካል የሆነው የግንባታ ፕሮጀክት በአማራ ክልል በ5 ዞኖች እና በ27 ወረዳዎች የሚከናወን ፕሮጀክት ነው፡፡ ከሰሞኑ የዞንና የወረዳ ኃላፊዎች በተገኙበት በ2012 ዓ.ም በሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮጀክት የተገነቡ የዳስና ከዳስ ያልተናነሱ የመማሪያ ክፍሎችን ግንባታ የተመለከተ ውይይት በጎንድር ከተማ ተካሂዷል፡፡
ባለፈው ዓመት ከፌደራል መንግስት በተመደበ 98 ሚሊየን ብር የተገነቡ ባለ አራት መማሪያ ክፍል ያላቸው 76 ብሎኮች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ግንባታቸው መጠናቀቃቸው የተሻለ አፈፃፀም እንደነበረው በውይይቱ ተነስቷል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉት ኃላፊዎች ፕሮጀክቱ ውጤታማ እንደነበርና ትምህርት የተወሰድበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በትምህርት ቤቶች የነበረውን የመማሪያ ክፍል ችግር የፈታና የስራ እድል ከመፍጠሩ በተጨማሪ ለህብረተሰቡ መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑንም የውይይቱ ተሳታፊዎች አክለው ገልጸዋ፡፡
በውይይቱ የተገኙት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ይልቃል ከፋለ (ዶክተር) ግንባታው የሚካሄደው በኢንተር ፕራይዞች በመሆኑ ለብዙ ወጣቶች የስራ ዕድል የፈጠራ ነው ብለዋል፡፡የህብረተሰቡን ተሳትፎ እና ሴፍትኔትን በመጠቀም ኢንተርፕራይዞኖች ውጤታማ እንዲሆኑ እገዛ ያስፈልጋቸዋል ያሉት ኃላፊው የህብረተሰቡና የአመራሩ ድጋፍና ክትትል እንደሚያስፈልግ ገልፀዋ፡፡
በተመሳሳይ በ2013 ዓ.ም ከፌደራል መንግስት በተመደበ 47 ሚሊየን ብርና በክልሉ መንግስት በተመደበ 10ሚሊየን ብር 41 ብሎኮችን ለመገንባት ወደ ስራ መገባቱን ከቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
