የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በክልሉ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በውጤታማነት ለማጠናቀቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በባህርዳር ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
በምክክር መድረኩ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች ፣ የትምህርትና የፀጥታው መዋቅር እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ትምህር ቢሮ ኃላፊ ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በተለያዩ ምክኒያቶች መዘግየት በተማሪዎች ላይ የስነልቦና ጫና እንደፈጠረባቸው የተናገሩት ኃላፊው ቀጣዩን ፈተና በተረጋጋ መንፈስ እንዲፈተኑ ሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ተማሪዎች በስነልቦና የጠነከሩ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የፈተና ሂደቱ ውጤታማ ይሆን ዘንድ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራ የሚጠይቅ ነው ያሉት ቢሮ ኃላፊው ፈተናውን ከማጓጓዝ ጀምሮ የፈተና ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን የፀጥታ መዋቅሩና ባለድርሻ አካላት ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡በየደረጃው ተመሳሳይ ውይይቶች እንደሚኖሩ ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ከኩረጃ የፀዳ የፈተና ስርአት እንዲኖር የፈተኝ መምህራንና ሱፕርቫይዘሮች ሚና የጎላ መሆኑን የተናገሩት ቢሮ ኃላፊው ኩረጃ ትውልድን የሚያጠፋ መጥፎ ተግባር በመሆኑ ወላጆችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ኩረጃን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙም ጥሪ ቀርቧል፡፡
የፀጥታ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች የፀጥታ መዋቅሩ ከዚህ በፊት ያለውን ልምድ በመጠቀም ሰላማዊ የፈተና ሂደት እንዲኖር በልዩ ትኩረት ይሰራል ተብሏል፡፡
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበረ አዳሙ በበኩላቸው ተማሪወች የረጅም አመት ውጤታቸውን የሚያዩበት ጊዜ በመሆኑ የፀጥታ መዋቅሩ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
በፈተና ዙሪያ ችግር ለመፍጠር የሚንቀሳቀስ ማነኛውን አካል አንታገስም ያሉት ኮሚሽነሩ የክልሉን ሰላም የማይፈልጉ አካላት ፈተናውን እንዳያደናቅፉ በቅንጅትና በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በተለይ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ልዩ የፀጥታ ሀይል ስምሪት ይደረጋል ያሉት ኮሚሽነሩ የፀጥታ ተቋሙ ችግሮች ሲፈጠሩ ፈጣን ውሳኔዎችን መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡
ፈተናውን የሚያውኩ ማነኛውን መረጃዎች ፈጥኖ ለፖሊስ መስጠት ከህብረተሰቡ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን አክለው ገልፀዋል፡፡
በመድረኩ የተሳተፉ አካላት ፈተናው በውጤታማነት እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ተማሪዎች በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሱና ትክክለኛ ምንጫቸው ከማይታወቁ መረጃዎች ራሳቸውን በመጠበቅ የተዘጋጁበትን ፈተና እንዲፈተኑም ተጠይቋል፡፡
በአማራ ክልል ከ82ሺህ በላይ ተማሪዎች በ255 የፈተና ጣቢያዎች እንደሚፈተኑ ይጠበቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *