የአብክመ ትምህርት ቢሮ በክልሉ ከሚገኙ መምህራን ትምህርት ኮሌጆች ጋር በቀጣይ ስራዎች ዙሪያ ውይይት አካሄደ
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከ10ሩ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ዲኖች ጋር በቀጣይ ስራዎችና በተመራቂ ተማሪዎች ዙሪያ ከሰሞኑ በእንጅባራ ከተማ ውይይት አድርጓል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ምክኒያት የተቋረጠው የመማር ማስተማር ስራ ኮሌጆች የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ተማሪዎች በአሉበት ትምህርቱን እንዲከታተሉ ከማድረግ ባሻገር መምህራን ትምህርት ኮሌጆች ለህብረተቡ ግንዛቤ በመፍጠር፣ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን በመስራትና የጥናትና ምርምር ስራዎችን በመስራት ላደረጉት ተሳትፎ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በቀጣይ ስራዎችና በተመራቂ ተማሪዎች ዙሪያ ትምህርት ቢሮው መነሻ ሀሳብ አቅርቦ ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡ በጎንደር መምህራን ትምህርት ኮሌጅ መምህራን ተነሳሽነት ተማሪዎች በአሉበት በቴክኖሎጅ ትምህርቱን ተደራሽ ለማድረግ የቀረበው የቴክኖሎጅ ሀሳብ የውይይቱ አንድ አካል ነበር፡፡
በቀረቡ መነሻ ሀሳቦች በተደረገው ሰፊ ውይይት የጋራ ሀሳብ መያዝ ተችሏል፡፡ በቀጣይ ከመንግስት በሚሰጠው አቅጣጫ መሰረት ትምህርት ሲከፈት በተለይ ለተመራቂ ተማሪዎች ያለው ጊዜ አጭር በመሆኑ ኮሌጆች ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ይገባቸዋል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል ኮሌጆች በክረምት የግንባታና የጥገና ስራዎቸ፣የአረንጓዴ ልማት ስራዎች፣ለመማር ማስተማር የሚያግዙ አማራጭ ቴክኖሎጅ ማዘጋጀት እንዲሁም በኮረና መከላከል ግንዛቤ ፈጠራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ሌሎች የክረምት ስራዎችም እንደወትሮው በታቀደላቸው ጊዜ እንዲሰሩ በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡
በቀጣይ የመማር ማስተማሩን ስራ ለማስጀመር፣ በተመራቂ ተማሪዎች ዙሪያና ትምህርቱን በቴክኖሎጅ ማዘመንን አስመልክቶ በቀጣይም ውይይቶች እንደሚኖር ታውቋል፡፡
