የእንጅባራ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ከ7 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ በጀት የተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ማከናወኑን አስታወቀ
የእንጅባራ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የክልልና የሁሉም ኮሌጅ ኃለፊዎች በተገኙበት ሰሞኑን ከ7 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ በጀት በኮሌጁ ውስጥ ያስገነባቸውን የቅድመ መደበኛ ትምህርት መስጫ እና የተሟላ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎችን አስመርቋል፡፡
7ኛውን የአማራ ክልል የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ የስፖርት ውድድር አዘጋጅ የነበረው የእንጅባራ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክኒያት ላልተወሰነ ጊዜ ቢራዘምም የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች ግንባታ ለቀጣይ የስፖርት ሳይንስ ትምህርትና ለተለያዩ ውድድሮች ያለው ጠቀሜታ የጎላ በመሆኑ ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ማጠናቀቁን የኮሌጁ ዲን አቶ ሽቱ አየን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ኮሌጁን በስፖርት ሳይንስ ትምህርት ሞዴል ለማድረግ ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን ዲኑ አክለው ገልፀዋል፡፡
ኮሌጆች ከተሰጣቸው ኃላፊነት አነዱ የሆነው የቅድመ መደበኛ መምህራንን ማሰልጠን ሲሆን ለዚህም የሚያግዝና የማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት ያግዘኛል ያለውን ሞዴል የቅድመ መደበኛ ማዕከል በመገንባት እጩ መምህራን ልምምድ የሚያደርጉበትና የኮሌጁ ሰራተኞችና የአካባቢው ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ህፃናትን የቅድመ መደበኛ ትምህርት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡
በምረቃ ስነስርአቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ይልቃል ከፋለ /ዶ.ር/ የእንጅባራ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የስፖርት ውድድሩን ምክኒያት በማድረግ ለኮሌጁ ቋሚ መሰረት የጣለ ስራ መስራቱ ለሌሎች ኮሌጆች ትምህርት ሰጭና ሊመሰገን የሚገባው ነው ብለዋል፡፡ በሁለቱም የመሰረት ልማት ስራዎች ውጤታማ በማድረግ ሚናቸውን ለተጫወቱ የኮሌጁ አመራሮች፣መምህራንና ሰራተኞች ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በቀጣይም ኮቪድን እየተከላከልን በክረምት ሌሎች የኮሌጁን ገጽታ የሚያሻሽሉ ስራዎችን በተቀናጀ ሁኔታ መስራት ይገባል ብለዋ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *