መስከረም 10/2013 ዓ.ም
ባህርዳር
በአማራ ክልል በሁሉም ትምህርት ቤቶች የነባር ተማሪዎች ምዝገባ ዛሬ ተጀምሯል፡፡
የ2013 የትምህርት ዘመን የነባር ተማሪዎች ምዝገባ ዛሬ ተጀምሯል፡፡ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ምዝገባ አስፈላጊውን ዝግጅት ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን ባለፈው ሳምንት የአዲስ ተማሪዎች ምዝገባ የተካሄደ ሲሆን ከዛሬ መስከረም 10-14/2013 ዓ.ም ጀምሮ የነባር ተማሪዎች የነፃ ዝውውር ካርዳቸውን በመውሰድ ምዝገባቸውን በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡
በባህርዳር ከተማ የሚገኘው አንጋፋው የጣና ሐይቅ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከፈተኛ የተማሪ ቁጥር የሚያስተናግድ ሲሆን በዛሬው እለት ከ9ኛ ወደ 10ኛ ክፍል የተዛወሩ ተማሪዎችን ብቻ ካርድ በመስጠት በመመዝገብ ላይ ነው፡፡ የትምህርት ቤቱ ም/ርዕሰ መምህር አቶ ፀጋየ ተፈራ በተማሪዎች ምዝገባ መጨናነቅ እንዳይፈጠር ፕሮግራም አውጥተው በመመዝገብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎች ወደ ምዝገባ በሚመጡበት ሰዓት ማስክ ለብሰው እንዲገቡ ይደረጋል ያሉት ም/ርዕሰ መምህሩ የንጽህና መጠበቂያዎች በትምህርት ቤቱ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችም ተማሪዎችን በማስተባበር ሲያስመዘግቡ ተመልክተና፡፡ መምህራንም በወጣው ፕሮግራም መሰረት ራሳቸውንና ተማሪዎችን ለመታደግ የኮሮና መከላከያ ህጎችን በመከተል በመመዝገብ ላይ ናቸው፡፡
