በአማራ ክልል ከደረጃ በታች ያሉ ትምህርት ቤቶችን ለማሻሻል ከ6 ሺህ የሚበልጡ የመማሪያ ክፍሎችን እየገነባ መሆኑን የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ፈንታ ገለፁ ።

በኮምቦልቻ ከተማ በሦስት ትምህርት ቤቶች ስድስት ህንጻዎች ለመገንባት ዛሬ የመሰረተ ድንጋይ ሲቀመጥ ህዝባዊ ውይይት ተካሔዷል ።

ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ መላኩ ፈንታ በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ ያሉ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማወቅ በ2011 ዓ/ም በተደረገ ጥናት 16 በመቶው ብቻ ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡

በሦስት ዓመት ውስጥ ወደ 55 በመቶ ለማሳደግ 21 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ህብረተሰቡን በማስተባበር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ በጀት ዓመትም ከአባላት በሚሰበሰብ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ከ6 ሺህ የሚበልጡ መማሪያ ክፍሎች የመገንባት ስራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ትምህርት ቤቶችን በአዲስ በመገንባትና ማስፋፊያ በማድረግ ደረጃቸውን ይሻሻላል ያሉት አቶ መላኩ ፤ ግንባታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ በኮሮና ምክንያት ስጋት የሆነውን የክፍል ጥበት ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ።

”የበለፀገች አገር ለመገንባት የተማረ የሰው ኃይል መፍጠር ይገባል” ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው ህብረተሰቡ የጀመረውን ተሳትፎ በማጠናከር የትምህርቱን ዘርፍ መደገፍ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ከትምህርት ዘርፉ በተጨማሪ የክልሉን ሁለንተናዊ ችግር በራስ አቅም ለመቅረፍ በውስጥና በውጭ ከሚኖሩ የክልሉ ተወላጆችና ባለድርሻ አካላት ጋርም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን አልማ ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ አበባው ታደሰ በበኩላቸው በዞኑ ካሉ 1 ሺህ 303 የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 17 በመቶው ብቻ ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡

የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ለማሻሻል ከዞኑ አስተዳደርና ከህብረተሰቡ ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በ103 ትምህርት ቤቶች ላይ የማስፋፊያ ግንባታ ለማከናወን መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ካሉ ከ750 ሺህ በላይ አባላትም ከ376 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ ግንባታው ይካሄዳል ብለዋል፡፡

ዛሬ ሦስት ትምህርት ቤቶችን ለማስፋፋት የ6 ህንጻ ግንባታ መሰረተ ድንጋይ ተቀምጧል ያሉት ደግሞ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ኢንጅነር ከማል መሃመድ ናቸው፡፡

ከአባላት በሚሰበሰብ 12 ሚሊዮን ብር አንድ ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ተገንብተው ለአገልግሎት እንዲበቁም ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል ፡፡

ከኮምቦልቻ ከተማ ባለሃብቶች መካከል አቶ አህመድ መሃመድ በሰጡት አስተያየት አልማ የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ለመገንባት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በመደገፍ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።

ለተጀመሩት ማጠናቀቂያና ለአዲስ ግንባታዎች ህብረተሰቡንና ተቋማትን በማስተባበር የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ ማቀዳቸውንም ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ከክልል፣ከደቡብ ወሎና ከኮምቦልቻ ከተማ የተውጣጡ አመራሮች፣ባለሃብቶች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣የሐይማኖት አባቶችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

የአማራ ልማት ማህበር/አልማ/ ከ4 ሚሊዮን በላይ አባላት እንዳሉት መረጃዎች ያመለክታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *