ከህዳር 17-18/2013ዓ.ም ለምዕራብ አማራ ዞኖች(ምስራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም እና አዊ ብ/አስ ዞን) 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ር/መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች በቀውስ ወቅት ትምህርትን መምራት በሚል ርዕስ እና የ2013 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ በእንጅባራ ከተማ ሲሰጥ የነበረው የግንዛቤ ማዳበሪያ ስልጠና ተጠናቋል፡፡ ስልጠናውን መነሻ በማድረግ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የትምህርት አመራሮችም ስልጠናው ወቅቱን የዋጀ፣ በቀጣይ ምን ምን ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገን መስራት እንዳለብን ያሳየና ስራችንን በተረጋጋ ስነልቦና እንድንመራ አቅም የፈጠረልን ነው ብለዋል፡፡ በአንድ በኩል ትምህርት ቤቶች በኮቪድ ተፅዕኖ ስር በመሆናቸውና ከዚህም ተፅዕኖ ያልተላቀቅን በመሆኑ በሌላ በኩል ወቅታዊ የሀገራችን የፀጥታ ሁኔታና መሰል ጉዳዮች ያሉበት ወቅት በመሆኑ ስልጠናው ለእኛ የትምህርት አመራሮች ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ በተያያዘም የኮቪድ ወረርሽኝ ፕሮቶኮሎች ጠብቀን ስራችንን ለመስራት በምናደርገው ጥረት የመምህራን ተባባሪነትና የስራ ተነሳሽነት እጅግ አስደናቂ ነበር ብለዋል፡፡ በዚህም መምህራን ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል ተብሏል፡፡ ሆኖም ግን በትምህርት ሚኒስቴር በኩል በወቅቱ ለተማሪዎች ይቀርባል የተባለው የተማሪዎች ማስክ አለመቅረቡ በቀጣይ መስተካከል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በአንዳንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመብራት ችግር እንዳለ ገልፀው አንዳንዶች ደግሞ ችግሩን ለመቅረፍ ትራንስፎርመር ግዥ ለመፈፀም ገንዘቡን ለመብራት ሃይል ቢከፍሉም ትራንስፎርመር በወቅቱ እንዳልቀረበላቸው አንስተዋል፡፡ ውይይቱን የመሩት የአብክመ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ሲያጠቃልሉ አሁን ያለንበት ጊዜ ቀውስ ወቅት በመሆኑ ለቀውስ ወቅት የሚመጥን አመራር መስጠት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ የአማራ ክልል ትምህርት ቤቶች ችግር ይታወቃል ያሉት ሃላፊው ችግሮችን ለመፍታት ወደ ውስጣችን በመመልከት ችግሮችን መፍታት አለብን ብለዋል፡፡ ችግሮችን ውጫዊ ካደረግናቸው በእጃችን ያለውን አቅም ማየት አንችልም ብለዋል፡፡ ለዚህም መምህራንና የአካባቢውን ማህበረሰብ በማስተባበር የትምህርት ቤት ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ ሆኖም ግን ከተማሪዎች መቀመጫ ወንበር አኳያ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እያደረግን ነው ያሉት ሃላፊው ትምህርት ሚኒስቴር የመደበውን ጨምሮ ትምህርት ቢሮ ከ200ሚሊየን ብር በላይ በጀት በመመደብ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እያደረገ እንዳለ ገልፀዋል፡፡ ከኮቪድ አኳያም በፕሮቶኮሉ መሰረት አሁን እያደረግነው ያለውን ጥረት አጠናክረን መቀጠል አለብን ያሉት ሃላፊው ሁሉም ተማሪዎች አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እንዲለብሱ በማድረግ ረገድ ትምህርት አመራሩ ስራ መሆን አለበት ብለዋል፡፡ ከወቅታዊ ሀገራችን ሁኔታ አኳያም መምህራንና የትምህርት ማህበረሰቡ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀው ድጋፉ በቀጣይም በተደራጀ አግባብ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡ በትምህርት ቤቶች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ እንዲሰፍን ትኩረት እንዲሰጠው ያሳሰቡት ሃላፊው በስልጠና ወቅት ሰልጣኞች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ገንዘብ ማዋጣታቸው እንዳስደሰታቸው የገለጹት ዶ/ር ይልቃል የተዋጣውን ገንዘብም ስልጠናው በሚካሄድበት በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ የባንክ አካውንት በኩል ገቢ ተደርጎ ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና ለአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ እንዲደርስ ይደረጋል ብለዋል፡፡