በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን 26 ሚሊዮን ተማሪዎች እንዲሁም በአማራ ክልል 6 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ርቀዉ መቆየታቸውን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ አበበ (ዶክተር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከጥቅምት 9/2013 ዓ.ም ጀምሮ በጤና ሚኒስቴር ምክረ ሀሳብ መሠረት ቫይረሱን በመከላከል ትምህርት እንዲጀመር ቢደረግም መምህራንን ጨምሮ ተማሪዎች የተቀመጠውን የመከላከል መስፈርት እየጣሱ መሆኑ ዶክተር ሙሉነሽ አስገንዝበዋል፡፡
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በአግባቡ አለመጠቀም፣ ርቀትን አለመጠበቅ እና የንፅህና መጠበቂያ አለመጠቀም በተማሪዎች እንዲሁም በመምህራንም እንደሚስተዋል ተናግረዋል፡፡ ትምህርት ቤቶችን ለመከታተል የተቋቋመው ግብረ ኃይል ባደረገው ግምገማ ይህንኑ ክፍተት ማስተዋሉን ዶክተር ሙሉነሽ ተናግረዋል፡፡
“በትምህርት ቤቶች የሚስተዋለው ችግር የተገኘውን ግብዓት በአግባቡ አለመጠቀም መሆኑን በተደረገው ግምገማ ተለይቷል፡፡ የመማሪያ ክፍሎች በተቀመጠው ስታንዳርድ አለመሥራት፣ ተማሪዎች ርቀታቸውን አለመጠበቅ፣ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብልና የንፅህና መጠበቂያ አለመጠቀም በብዙ ትምህርት ቤቶች ይስተዋላል፡፡ ትምህርት ቤቶች ይህን ክፍተት ማሟላት እንዳለባቸው ማሳሰብ የመግለጫው አላማ ነው” ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ይህ ክፍተት በሁሉም ትምህርት ቤቶች እንደማይስተዋልና ጠንካራ ትምህርት ቤቶች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡
አንድ ተማሪ ወይም መምህር በቫይረሱ ተያዘ ማለት መላው ማኅበረሰብ እንደተጎዳ ይቆጠራል ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ተማሪዎች፣ መምህራንና የትምህርት ቤት አስተዳደሮች የኮሮና ቫይረስን ከመከላከል አንፃር አርዓያ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡
ወላጆችና መላው ማኅበረሰብም ልጆቻቸውን መምከር እንደሚጠበቅባቸውም ዶክተር ሙሉነሽ በመግለጫቸው አስገንዝበዋል፡፡
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሚያደርሰው ጉዳትና ሞት እየጨመረ ቢመጣም መላው ማኅበረሰብ እየተዘናጋ በመምጣቱ ትምህርት ቤቶችም ወረርሽኙን ከመከላከል አንፃር ክፍተት እንዳለባቸውና በፍጥነት ሊያስተካክሉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በተለያየ ምክንያት ለ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የተመዘገቡ ተማሪዎች እና በትምህርት ገበታቸው የተገኙ ተማሪዎች ቁጥር ዝቅተኛ ነው ፤ ይህም ከባለፈው የትምህርት ዘመን አንፃር የቀነሰ እንደሆነ ዶክተር ሙሉነሽ ገልፀዋል፡፡
በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በኮሮናቫይረስ ምክንያት የመማር ማስተማር ሂደት በመቋረጡ በርካታ ሴት ተማሪዎች ለጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መጋለጣቸውን ዶክተር ሙሉነሽ በሰጡት መግለጫ አስታውሰዋል፡፡
ተማሪዎች በወቅቱ እንዲመዘገቡና በትምህርት ገበታቸው ተገኝተው በአግባቡ እንዲማሩ ወላጆች፣ የወጣቶች ማህበራት፣ ታዋቂ ሰዎች፣ እድሮች፣ ባለሀብቶች ብሎም መላው ማኅበረሰብ ርብርብ እንዲያደርግ ዶክተር ሙሉነሽ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘገባው የአማራ ብዙሐን መገናኛ ድርጅት ነው።
