የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከታህሳስ 1-2/2013 ዓ.ም የወረዳና የዞን የትምህርት አመራሮችና የመምህራን ማህበር አመራሮች በተገኙበት ቀውሱን ግምት ውስጥ ያስገባ የትምህርት አመራር መስጠት በሚቻልበትና በቀጣይ የትምህርት ዘመኑ ዋና ዋና ተግባሮች ዙሪያ ትኩረት ያደረገ የምክክር መድረክ በባህርዳር ከተማ ተካሄደ፡፡
በቀውስ ወቅት ትምህርት እንዴት ሊመራ ይችላል በሚልና በ2013 የትምህርት ዘመን ዋና ዋና ተግባራት ላይ ትኩረት ያደረጉ መነሻ ጹሁፎች በቢሮ አመራሮች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በክልሉ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ በሆኑ ችግሮች የትምህርት ስርአቱ በእጅጉ ችግር የገጠመው ቢሆንም መምህራን፣ የትምህርት አመራሩ እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ባካሄዱት ርብርብ ትምህርት ማስቀጠል መቻሉ ተነግሯል፡፡ አሁንም በተለያዩ ምክኒያቶች በርካታ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አለመምጣታቸው የተገለፀ ሲሆን ሁሉም አካላ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል ተብሏል፡፡
ወቅታዊ ችግሩን ግምት ውስጥ ያስገባ አመራርና አደረጃጀት በትምህርት ተቋማት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ይልቃል ከፋለ/ዶክተር/ ተለማጭ/Flexible/ የሆነ የአመራር ዘይቤ መከተል እንደሚገባ ተናግረዋል:: እስካሁን በተካሄዱት ተግባራት የተሳተፉ አካላትን ያመሰገፈኑት ቢሮ ኃላፊው ከሳምንት በኃላ የሚሰጠውን የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ያለምንም ችግር እንዲፈፀም ከወዲሁ አስፈላጊው ዝግጅት እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡
የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወትሮው በተለየ በኦንላይ የሚሰጥ በመሆኑ ልዩ ጥንቃቄ ተደርጎበት ይሰራል ብለዋል፡፡
የትምህርት ስርአቱ በችግር ውስጥ ቢሆንም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመረውን መልካም ተግባር አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ያሉት ቢሮ ኃላፊው ከአልማ ጋር የተጀመረውን የትምህርት ቤቶች ግንባታ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶች ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በትምህርት ቤቶች ኮቪድን እየተከላከሉ መማር ማስተማሩን ውጤታማ ለማድረግ ማስክ መልበስና ሌሎችን ጥንቃቄዎች መተግባር ግድ መሆኑም በመድረኩ ተገልጧል፡፡
በመድረኩ የተሳተፉ የትምህርት አመራሮች በቀውስ ጊዜ ትምህርትን ለመምራት በሚቻልበት ሁኔታ የተሰጠው ስልጠና እና ወቅቱን ግምት ውስጥ ያስገባ ውይይት ማድረጋችን በቀጣይ ስራዎች በቂ ግንዛቤ መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡ በትምህርት ስርአቱ እንዲህ አይነት ተደራራቢ ችግሮች ተከስተው የማያውቁ በመሆኑ አስቸጋሪ ወቅት ቢሆንም ከመምህራኖቻችን ጋር በመሆኑን እንወጣዋለን ብለዋል፡፡
የተፈጠረውን ቀውስ ግምት ውስጥ ያስገባ አመራር በመከተል የክልሉን ትምህርት ለመታደግ ከምን ጊዜውም በላይ መስራት እንደሚገባና ከወትሮው የተለየ የአመራር ጥበብ መከተል የክልሉን ትምህርት መታደግ እንደሚገባም በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡
ህግን በማስከበር ላይ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት፣ለአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ መምህራን፣የትምህርት ባለያዎችና አመራሩ ላደረጉት ድጋፍ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አመስግነዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *