በአማራ ክልል በሚገኙ አስር መምህራን ትምህርት ኮሌጆች ለተከታታይ ሶስት አመታት በመደበኛዉና በማታዉ መርሃ ግብር በዲፕሎማ ትምህርታቸዉን ሲከታተሉ የቆዩ ተመራቂ ተማሪዎች የብቃት መለኪያ ምዘና ፈተና ወስደዋል፡፡
በፈተናዉ ወቅት ተገኝተን ያነጋገርናቸዉ ተፈታኞችም የምዘና ፈተናዉ ለሙያዉ ብቁ መሆን አለመሆናቸዉን መለካት የሚያስችል መሆኑን ነግረዉናል፡፡ ከተፈታኞች መካከል የሆነዉ መልካሙ ታደሰ የምዘና ፈተናዉ ለተከታታይ ሶስት አመታት በኮሌጅ ቆይታቸዉ ከተማሩት ትምህርት ተዉጣጥቶ የተዘጋጀ በመሆኑ ለሙያዉ ያለዉን ብቃት መለካት የሚያስችል መሆኑን ተናግሯል፡፡ የምዘና ፈተናዉን የወሰደችዉ ከተማ አስማረ በበኩሏ ከፈተናዉ ጥሩ ዉጤት እንደምትጠብቅ ገልጻ የሙያዎች ሁሉ እናት ወደሆነዉ የመምህርነት ሙያ ተሰማርታ ብቁ ዜጋ ለማፍራት ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች፡፡
የመምህራንና ትምህርት ቤት አመራሮች የሙያ ፈቃድ አሰጣጥና እድሳት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ይገርማል አያሌዉ ፈተናዉ ተማሪዎች በኮሌጅ ቆይታቸዉ ምን ያህል ለሙያዉ ብቁ መሆናቸዉን ለመለካት መዘጋጁት ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የፈተናዉን ዉጤት መሰረት በማድረግ በተለያዩ መመዘኛዎች ትንታኔ እንደሚሰራበት ተናግረዋል፡፡ ይህም ከኮሌጅ ኮሌጅ ከትምህርት ክፍል ትምህርት ክፍል በሴቶችና በወንዶች መካከል ያለዉን ልዩነት ለማወቅ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ልሳነወርቅ ተስፋሁን ምዝናዉ በስልጠና ስርዓቱ ያለፉ ተማሪዎች ብቃትና አስልጣኝ ተቋማት የሚገኙበትን ደረጃ ለማወቅ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡ አስልጣኝ መምህራን ትምህርት ኮሌጆችን ለመለዬት እንደ አንድ መመዘኛ በመሆን እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡ በዚህም ተቋማት ወደፊት የስልጠና ሂደታቸዉን እንዲፈትሹ ያደርጋል፡፡ እንደ ክልል ብሎም እንደ ሀገር የመምህርን ስልጠና ያሉበትን ተግዳሮቶች ለመለዬትና ችግሮችን ሊፈቱ የሚችሉ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለመተግበር ያግዛል፡፡ የስርዓተ ትምህርት ክለሳ ለማድረግ ሲታሰብም በምዘናዉ የተገኙ ዉጤቶች እንደ አንድ ግብዓት ሆኖ እንደሚያገለግል አቶ ልሳነወርቅ ተስፋሁን ገልጸዋል፡፡
ተመዛኝ ተማሪዎች 70 እና ከዛ በላይ ካስመዘገቡ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የሚሰጣቸዉ ይሆናል ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *