ሀገር ውጤታማ መምህርና የማይሸነፍ ወታደር ሲኖራት ከፍ ትላለች፡፡ መምህሩ ያስተምራል ወታደሩ ይጠብቃል፡፡ መምህር ከሌለ ያወቀና የሚመራመር ትውልድ አይኖርም፣ ወታደር ከሌለ በሰላም የሚኖሩባት ሀገር አትኖርም፡፡
የአማራ ክልል መምህራን ማሕበር ጠላትን መክተው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ላኮሩት የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ድጋፉ የተደረገው ከወረዳ እስከ ክልል ባሉ የመምህራን ማሕበር የተውጣጣ ነው፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት የአማራ ክልል መምህራን ማሕበር ፕሬዝዳንት እናውጋው ደርሰህ ሀገር የካዱት ወንበዴዎች ከእንስሳዊ ባሕሪ ያነሰ ድርጊት ማሳዬታቸውን ተናግረዋል፡፡ ትህነግ የፈፀመችው እኩይ ድርጊት በአስቀያሚ ታሪክ ውስጥ የማይረሳ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ድርቱ ከኢትዮያዊያን ባሕል የወጣና አሳፋሪ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ትህነግ በመከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኃይላና ሚሊሻ በተደረገ ጀብዱ መደቆሷን ተናግረዋል፡፡ ይህም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም፣ መረጋጋትንና እፎይታን ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡
መምህራን ጀብዱ ለፈጸሙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ልዩ ክብር አለን ብለዋል፡፡ ለጀግኖቻችን ድጋፍ ስናደርግም ኩራት ይሰማናል ነው ያሉት፡፡ ሰራዊታችን ድል እንዳደረገ ሁሉ መምህራንም የመማር ማስተማሩ ሂደት ውጤታማ እንዲሆን እንሰራለን ብለዋል፡፡
የተደረገው ድጋፍ 627 ሺህ 100 ብር ወጪ የተደረገበት የቁሳቀስ ድጋፍ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ መምህራን ለሀገር አለኝታዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ይቀጥላሉም ብለዋል፡፡
የደቡብ ወሎ መምህራን ማህበር ሊቀመንበር መኮንን ጌታቸው ሀገር አደጋ ላይ ስትወድቅ ታሪክ የሰሩ የእኛው ውጤቶች ናቸው ብለዋል፡፡ ጀብደኞቹ ለእኛው ዘብ ሆነው ቀና ብለን እንድንሄድና የኢትዮጵያ አንድነት እንዲቀጥል አድርገዋል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያን ተፀይፎ ኢትዮጵያን የመራው ቡድን መምራት ሲያቅተው የፈፀመው የክህደት ተግባር የሚያሳዝን መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
ጀግኖቹ ኢትዮጵያን አስቀጥለዋል፣ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሚነሱ አካላትም እንደሚፈራረሱ ምስክሮች ሆነዋል ነው ያሉት፡፡
ድጋፉን የተቀበሉት የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባላት እየተደረገልን ላለው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ማህበረሰቡ እያደረገው ያለው ድጋፍ ሞራል እንደሆናቸውም ገልጸዋል፡፡
በድጋፍ ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደረጃ የማህበራዊ ክላስተር አስባባሪና የሰራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ የመምህራን ማሕበሩ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻው ከከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት አንጻር የሚደረገው ድጋፍ ትንሽ ነው ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ነገር ግን ማሕበረሰቡ እያሳዬው ያለው ድጋፍ የክልሉን መንግሥት አኩርቷል ብለዋል፡፡
ማህበረሰቡ የሚያደረገውን ድጋፍ እንዲቀጥል የጠቀየቁት ዶክተር ሙሉነሽ የክልሉ መንግሥትም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውዋል፡፡ ሌሎች ማህበራትም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ መምህራን፣ የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎችም ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡