በ10 ዓመቱ የትምህርት ልማት እቅድ ዙሪያ ውይይት ተካሄደ
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከሁሉም ዞንና ከተማ አስተዳደሮች ከተውጣጡ የእቅድና መረጃ ቡድን መሪዎችና ባለሙያዎች ጋር በደብረታቦር ከተማ ውይይት አካሂደዋል፡፡
በቀጥታ ፈፃሚ ከሆኑት ቡድን መሪዎችና ባለሙያዎች ጋር ውይይቱ መካሄዱ ለቀጣይ እቅዱን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያግዝ የተገለፀ ሲሆን በቀረበው እቅድ ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደርጎ የጋራ መግባባት ተደርሶበታል፡፡
የቢሮው እቅድና መረጃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ምስጋናው አማረ በየደረጃው ያለው የዘርፉ ባለሙያ የተናበበ እቅድ እንዲኖርና የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ጠቃሚ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል በየደረጃው የተዘጋጀውን እቅድ ለባለድርሻ አካላት ተደራሽ በማድረግና ግንዛቤ በመፍጠር ሁሉም ባለድርሻ አካል የተሳተፈበት ክልላዊ የትምህርት ልማት እቅድ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉት ቡድን መሪዎችና ባለሙያዎች በበኩላቸው ሰነዱ የ10 ዓመት የትምህርት ልማት እቅድ እንደመሆኑ መጠን ሰፊ ውይይት ማድረጋችን የጋራ መግባባት እንድንፈጥር ከማገዙ ባሻገር ተሞክሮ የተለዋወጥንበትና በአጠቃላይ እቅዱን ለማሳካት ግልፀኝነት የፈጠርንበት ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በመድረኩ የተሳተፉ ቡድን መሪዎችና ባለሙያዎች በየደረጃው የሚገኘው የእቅድና መረጃ ክፍል ሰፊና ውስብስብ ስራዎችን የሚሰራና ለዘርፉም የጀርባ አጥንት ሆኖ እያለ በጅኤጅ የተሰጠው ደረጃ ሞራል የሚነካ ነው ብለውታል፡፡ ስራችን በአግባቡ እየተገበርን ለረጀም ዓመታት ጥያቂያችን ብናቀርብም መልስ ማግኘት አልቻልንም ያሉት ተሳታፊዎች በመድረኩ መጨረሻ በቢሮ ዓመራሮች መልስ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ነበር፡፡
የተሳታፊዎችን ጥያቄ በማክበር በመድረኩ ማጠናቀቂያ የተገኙት የአማራ ክልል ትምህር ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ መኳንት አደመ ዘርፉ ለትምህርት ተቋሙ ወሳኝ ክፍል መሆኑ አይካድም ያሉት ም/ኃላፊው እንደሌሎቹ ክፍሎች ሁሉ ድጋፍና ክትትል ይደረግለታል ብለዋል፡፡ የደረጃ ማነሱና ስራውን የማይመጥን መሆኑን ቢሮው ተረድቶ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ለማስተካከል ሰፊ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥ መልስ ለመስጠት ከሚመለከተው አካል ጋር ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን የተናገሩት ኃላፊው ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ስራችሁን በተለመደው ሁኔታ በትኩረት በመስራት የትምህርት እቅዳችን ለማሳካት ከምንጊዜውም በላይ በቅንነት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡ ቢሮውም በየደረጃው ላሉ ባለሙያዎችና ቡድን መሪዎች ቅሬታቸውን ለመፍታት ከሚመለከተው አካል ጋር የጀመረውን ስራ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *