በ13.5 ሚሊየን ብር ወጭ የተገነባው ደባርቅ ብርሃን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 18 መማሪያ ክፍሎች፣ቤተመፀሀፍት፣ቤተሙከራዎች፣የአስተዳደር ህንፃ፣መጸዳጃ ቤትና ክሊኒክ ያሟላ ነው፡፡
የደባርቅ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን ፈንታ በቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው የተገነባው ዘመናዊ ትምህርት ቤት በከተማው የሚታየውን የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ችግር የሚፈታ ነው ብለውታል፡፡
የትምህርት ቤቱ ግንባታ ዘመን ተሻጋሪ እና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ጥራት ያላቸውን የግንባታ ቁሳቁሶችን ከመጠቀም ጀምሮ ተገቢ የሆነ የባለሙያ ክትትል ተደርጎለታል ተብሏል፡፡
የግንባታ ሂደቱ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን በቀጣይ ወር ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው ያሉት ኃላፊው የመምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ቅጥርም እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ችግሩን በመረዳት እድሉን መስጠቱ በከተማ አስተዳደሩ ተማሪዎችና መምህራን ስም ምስጋና ያቀረቡት የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ ትምህርት ቤቱ አዲስ በመሆኑ የተማሪዎች መቀመጫ ወንበርና ሌሎች ግብአቶችን ለማሟላት ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህን ዘመናዊ ትምህርት ቤት ግብአት ለማሟላት በሚደረገው ጥረት የሚመለከተው የመንግስት ተቋም፣የአካባቢው ማህበረሰብና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጽ/ቤቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በከተማው የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በከተማ አስተዳደሩ፣በሊማሊሞ ቻሪቲና ከአለም ባንክ በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
አልማ በከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻለ የሚሰራው ስራ ውጤታማ እንዳልሆነም ተጠቁሟል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *