የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2013ዓ.ም በክልሉ በጀት በሚገነቡ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና ከፌደራል ትምህርት ሚኒስቴር በተገኘ የጂኢኩፕ በጀት በሚሰሩ ፈርኒቸሮች ስራው በወቅቱና በጥራት በሚሰራበት ሁኔታ ከክልሉ የሙያና ቴክኒክ ኢንተርፕራይዝ ቢሮ፣ ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊዎች፣ ዞን ሙያና ቴክኒክ ሃላፊዎች፣ ግንባታ በሚካሄድባቸው ወረዳዎች የወረዳ አስተዳዳሪዎችና ትምህርት ጽ/ቤት ሃላፊዎች፣ የዞንና ወረዳ ግንባታ ባለሙያዎች ጋር ጥር 14/2013ዓ.ም በፍኖተ ሰላም ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
በ2013ዓ.ም በሚሰሩ ፈርኒቸሮች ዙሪያ የውይይት መነሻ ፁሁፍ ያቀረቡት የትምህርት ግብዓት አቅርቦትና ስርጭት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ይርሳው ብርሃኔ ሲሆኑ በሀገራን በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች የኮቪድ ፕሮቶኮሎችን ጠብቀው እንደገና እንዲከፈቱ ሲደረግ በትምህርት ቤቶች በተወሰነ ደረጃ የተማሪዎች መቀመጫ ወንበር እጥረት ማጋጠሙን ጠቅሰው ነገር ግን ቢሮው ባለፊት 3 ዓመታት የፈርኒቸር እጥረት ችግርን ለማቃለል ባደረገው ጥረትና በተቀመጡ አማራጭ መፍትሄዎች ችግሩን ማቃለል ተችሏል ብለዋል፡፡ በ2013ዓ.ም በኢንተርፕራይዞች የሚሰሩ ፈርኒቸሮች በጥራትና በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁና ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውሉ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ከዚህ በፊት የነበሩ እጥረቶችንና መልካም ተሞክሮዎችን አቅርበዋል፡፡ የክልሉ ትምህርት ቢሮም ባለፊት 4ዓመታት ከ500ሚሊየን ብር በላይ ለፈርኒቸር ስራ በጀት በመመደብ ከ283 በላይ ኢንተርፕራይዞችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በ2013ዓ.ም የሚገነቡ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ አስመልክቶ የውይይት መነሻ ጹሁፍ ያቀረቡት የቢሮው የሲቪል ምህንድስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ገበየሁ በተያዘው በጀት ዓመት የሚገነቡት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለ64 ኢንተርፕራይዞችና 320 ምሩቃን የስራ እድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን ገልፀው ተግባሩ ግን ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚሻ አስረድተዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የአብክመ ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ አረጋ ከበደ እንደገለጹት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2013ዓ.ም የሚሰሩ ፈርኒቸሮችና ግንባታዎች ጥራታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ የምክክር መድረኩን ማዘጋጀቱን አመስግነው ትምህርት ቢሮው የግንባታና መሰል ስራዎችን በጥቃቅን በተደራጁ ወጣቶች እንዲሰሩ ማድረጉ ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ግንባር ቀደም ነው ብለዋል፡፡ ከድጋፍና ክትትል ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮችንም በጋራ እየተመካከሩ ለመፍታትና የባለሙያ ስምሪትም እንደሚያደርጉ ሃላፊው ገልፀዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ በውይይቱ ማጠቃለያ እንደተናገሩት በመድረኩ በርካታ ተሞክሮዎች የተገኙበት መሆኑን አውስተው በጋራ ተቀራርቦ በመስራት የሚያጋጥሙን ችግሮችን ማቃለል እንችላለን ብለዋል፡፡ ስራዎቻችንን በትጋት፣ በመደጋገፍና በተነሳሽነት መንፈስ መስራት ከተቻለ ከግንባታ ጋር ያሉ ማነቆዎችን መፍታት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡ በክልሉ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተደራሽነት ችግር አለ ያሉት ሃላፊው የአማራ ክልል ባለው የህዝብ ቁጥር መጠን በቂ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አልተገነቡልትም ብለዋል፡፡ የክልሉ መንግስት ካለበት የበጀት እጥረት አኳያ በ2013 ለ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ የመደበው 88 ሚሊየን ብር ብቻ ነው ያሉት ሃላፊው ይህ ገንዘብ በምህንድስና ግምት መሰረት ከ8 ትምህርት ቤቶች በላይ ማሰራት ስለማይችል ወረዳዎች ግማሽ በጀቱን እንዲችሉ በማድረግ የትምህርት ቤቶችን የግንባታ ቁጥር ወደ 16 ለማሳደግ እንደታቀደ ገልጸዋል፡፡ ይህም ሆኖ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥር ከሌሎች ክልሎች አኳያ ተወስዶ ሲነጻጸር በቂ ስላልሆነ በቀጣይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *