የሃይሌ ሚናስ አካዳሚ በ2010 ዓ.ም ነበር በ12 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ለመገንባት ታቅዶ ወደ ሥራ የተገባዉ፡፡ ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ የመጀመሪያ ዙር ግንባታዉን ሙሉ በሙሉ ያጠናቀቀዉ አዳሪ ትምህርት ቤቱ 35 ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ጀምሯል፡፡
ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ ያሉ ተማሪዎች በአዳሪ ትምህርት ቤቱ የመማር እድል እንዳላቸው የትምህርቤቱ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ክፍሌ ተናግረዋል፡፡ ከመላ ሃገሪቱ የተውጣጡና ከስድስተኛ እና ከሰባተኛ ክፍል የተሻለ ዉጤት አስመዝግበዉ የአካዳሚዉን መግቢያ ፈተና የሚያልፉ ተማሪዎች ወደ አካዳሚዉ ይቀላቀላሉ፡፡
ዳይሬክተሩ አቶ ተስፋዬ ክፍሌ ለአብመድ እንደገለጹት ከሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች የተወጣጡ 35 የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎች አካዳሚዉን ተቀላቅለዉ ትምህርት ጀምረዋል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽ በመከሰቱ ምክንያት እንጅ የተማሪዎችን ቁጥር መጨመር ይቻል እንደነበርም ገልጸዋል፡፡
ከ9 እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ በእዉቀት፣ በክህሎት እና በሥነ ምግባር በማነጽ ሃገር ገንቢ ትዉልድ ለመፍጠር ያለመዉ አካዳሚዉ በሚቀጥለዉ ዓመት የቅበላ አቅሙን በመጨመር ከ100 በላይ ተማሪዎችን ያስተናግዳል ብለዋል፡፡ በአካዳሚው መሟላት የሚገባቸዉ ጅምናዚም፣ የተለያዩ ስፖርት ሜዳዎች፣ የመምህራንና የተማሪዎችን መኖሪያን ጨምሮ ሁሉም ግንባታዎች በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
የአካል ጉዳት ያለባቸዉ ተማሪዎችን ግንዛቤ ዉስጥ በማስገባት የተገነባዉ አዳሪ ትምህርት ቤቱ አቅም በፈቀደ መንገድ ዘመናዊ መሆኑን አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የመምህራን መኖሪያ፣ መማሪያ ክፍሎች፣ የተማሪዎች መመገቢያና ማረፊያ ክፍሎች ሙሉ በሙሉ ተገንብተዉ ተጠናቀዋል፡፡
በ2014 ዓ.ም ሁሉም ግንባታዎች ተጠናቀዉ አካዳሚዉ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ይገባል ተብሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *