በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው “እንድናገለግልዎ ማስክ ያድርጉ” መርሀ ግብር በአማራ ክልል በባህርዳር ከተማ በሚገኘው የባህርዳር መሰናዶ ትምህርት ቤት ዛሬ በይፋ ተጀምሯል፡፡
በንቅናቄ መድረኩ ከክልሉ ትምህርትና ጤና ቢሮ የሚመለከታቸው አካላት፣ በባህርዳር ከተማ የሚገኙ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራንና ሱፐር ቫይዘሮች እንዲሁም የትምህርት ቤቱ መምህራንና ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ለዓለም ጥላሁን እንደገለጹት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው “እንድናገለግልዎ ማስክ ያድርጉ” መርሀግብር ተግባራዊ በማድረግ የመማር ማስተማሩን ሂደት ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡ በተለይ ተማሪዎች መምህራኖቻችሁ እንዲያገለግሏችሁ ማስክ በአግባቡ መጠቀም ይገባል ያሉት መምሪያ ኃላፊው በከተማው የሚገኙ የግልና የመንግስት ትምህርት ቤቶች ከዛሬ ጀምሮ ማስክን በአግባቡ መጠቀምና ኮሮናን ለመከላከል የወጡ ህግና ደንቦችን መተግበር እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ሙላው አበበ በኮሮና ውስጥ ሆነን ትምህርት ቤቶችን ስንከፍት ኮሮናን እየተከላከልን ትምህርት ለማስቀጠል ቢሆንም አሁን የሚታየው መዘናጋት ግን አሳሳሰቢ ነው ብለዋል፡፡
ተማሪዎች ህብረተሰቡን በማየት ማስክ አለመልበስ እየታየ መሆኑን የተናገሩት ም/ኃላፊው ተማሪዎችና መምህራን ለህብረተሰቡ ማስክን በመልበስና የኮሮና መከላከያ ህጎችን በማክበር አርአያ ልትሆኑ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ተማሪዎች መምህራን እንዲያገለግሏቸው ማስክን ሁሌና በአግባቡ መጠቀም ይገባቸዋልም ብለዋል፡፡
የባህርዳር መሰናዶ ትምህርት ቤትና የዶና በር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በትምህርት ቤታቸውና በጎዳና ላይ የተለያዩ መልዕክቶችን በመያዝ ለህብረተሰቡ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ በአማራ ክልል በሁሉም ትምህርት ቤቶች “እንድናገለግልዎ ማስክ ያድርጉ” መርሀግብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡